የኢትዮጵያ አየር መንገድ የድጅታል ካርጎ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2012( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው የካርጎ አገልግሎት ዲጂታል ስርዓት በመዘርጋት ለደንበኞቹ ምቹ ማድረጉን ገለፀ።

አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የሞባይል መተግበሪያ በመፍጠር ዘመናዊ የካርጎ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

በአንድሮይድም ሆነ በአይፎን ስልኮች መጫን የሚቻለው መተግበሪያው የካርጎና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ደንበኞች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተናግዱበት ምቹ አሰራር መፍጠሩንም አስታውቋል።

በመተግበሪያው ደንበኞች የበረራ ሰዓትን፣ የጭነት መረጃን፣ የጭነት የኪራይ አገልግሎት ጥያቄዎችን የሚለዋወጡበት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል 'ኢትዮጵያን ቻት-ቦት' የተሰኘው ሌላው መተግበሪያ ደግሞ በሜሴንጀርና ቴሌግራም መተግበሪዎች ወቅታዊና ፈጣን መረጃ የሚለዋወጡበት እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል።

ዓለም አይነተ ብዙ የዲጂታል አገልግሎች ወይም መተግበሪያዎችን የሚጠቀም በመሆኑ፣ የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም መተግበሪያዎችን በማበልጸግ ተቋማዊ አቅሙን በማጎልበት ለደንበኞቹ ምቹና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም