የጊኒ ዎርም በሽታ በተከሰተበት የጋምቤላ ክልል ቀበሌዎች የቤት ለቤት ቅኝት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የጊኒ ዎርም በሽታ በተከሰተበት የጋምቤላ ክልል ቀበሌዎች የቤት ለቤት ቅኝት ተካሄደ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2012 (ኢዜአ) የጊኒ ዎርም በሽታ በተከሰተባቸው የጋምቤላ ክልል ሁለት ቀበሌዎች ከ1 ሺህ 400 በላይ አባዎራዎችን ተደራሽ ያደረገ የቤት ለቤት ቅኝት መካሄዱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የበሽታውን ምልክት በማሳየት የተጠረጠሩ 91 ሰዎችን ደግሞ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ገብተዋል።
የጊኒ ዎርም በሽታ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1980ዎቹ በ21 አገሮች ተከስቶ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተይዘው ነበር።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 53 ሲሆኑ፤ የበሽታው ስርጭትም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት አፍሪካ አገሮች ብቻ ተወስኗል።
በቅርቡም በሽታው በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ዳግም መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የጊኒ ዎርም በሽታ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ አልተከሰተም።
ነገር ግን በነዚህ ዓመታት በሽታው የተገኘባቸው የቤት እንስሳት ነበሩ።
በኢትዮጵያ ደግሞ ለየት ባለ መልኩ የዱር እንስሳት ጭምር በበሽታው በመያዛቸው የቁጥጥር ሥራውን ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ቡድን ተዋቅሮ በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የቤት ለቤት ቅኝት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቅኝቱ አባዎራዎቹ ተደራሽ ከመሆናቸውም በላይ፤ ከመካከላቸውም የበሽታውን ምልክት በማሳየት የተጠረጠሩ 91 ሰዎች ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
በቅኝቱ የቤት እንስሳት ተደራሽ መሆናቸውን ዶክተር ኤባ ገልጸዋል።
በተጨማሪ በሽታው በተከሰተበት አካባቢዎች ለሚኖሩ ማህበረሰቦች የውሃ ማጣሪያ ቁሳቁስ ቀርበዋል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ተከናውነዋል።
በአካበቢው የሚገኙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የውሃ ኩሬዎችን መታከማቸውን አስረድተዋል።
ንጹህ የመጠጥ ውሃ በዘላቂነት በማቅረብ ችግሩን በቀላሉ መፍታት ይቻላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ሴክተሮች ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ችግሩን መፍታት ለጤና ሴክተር ብቻ የሚተው ኃላፊነት እንደማይሆን በማብራራት።
የጊኒ ዎርም እንቁላሉን ኩሬዎች ውስጥ የሚጥል ሲሆን፣ ሰዎች የኩሬውን ውሃ ሲጠጡ እንቁላሉን አብረው በመጠጣት በበሽታው ይያዛሉ፡፡
እንቁላሉም በሰውነት ውስጥ በመፈልፈል እስከ ሞት የሚያስከትል ጉዳት እንደሚያደርስ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።