በዓመቱ ከግብር ከፋዩ መሰብሰብ ከሚገባው ግብር 48 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም - ኢዜአ አማርኛ
በዓመቱ ከግብር ከፋዩ መሰብሰብ ከሚገባው ግብር 48 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ ከግብር ከፋዩ መሰብሰብ ከሚገባው ግብር ውስጥ 48 ቢሊዮን ብር አልሰበሰበም። በግብር አሰባሰብ ስራው በ11 ወራት 210 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም መሰብሰብ የተቻለው 162 ቢሊዮን ብር ነው። በመሆኑም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የግብር አሰባሰብ ስራውን በተገቢው መንገድ ማከናወን እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አሳስቧል። የምክር ቤቱ የገቢዎችና ጉምሩክ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የ2010 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ገምግሟል። የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ናፈቁሽ ደሴ እንደገለጹት፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ከግብር ከፋዮች መሰብሰብ የሚገባውን ያህል ግብር አልሰበሰበም። በ11 ወራት ከተሰበሰበው ግብር 70 በመቶ የሚሆነው የተሰበሰበ ቢሆንም የአሰባሰብ ስርዓቱ በታቀደው ልክና መሰብሰብ የሚገባውን ያህል አይደለም። "በዋናነት ባለስልጣኑ የታክስ የልማት ሰራዊቱን በአመለካከትና በአስተሳሰብ በተሟላ መንገድ መገንባትና መቅረጽ ባለመቻሉ የሚፈለገውን ውጤት ላለመምጣቱ ምክንያት ነው" ብለዋል። ይህም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች ባለመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአቅም ውስንነት ሳይገድበው ባለው አቅምና በተሰጠው ሃላፊነት ድርሻውን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው በሽያጭ መሳሪያዎች የቴክኒክ ምርመራና እድሳት ላይ ያከናወናቸው ተግባራት፣ በኦዲት ስራዎች እንዲሁም ሃሰተኛ ደረሰኞችን ሲጠቀሙ የነበሩ 265 ድርጅቶችን እንዲቀጡ በማድረግ ረገድ የተሰሩ ስራዎችን በጥንካሬ ገምግሟል። በባለስልጣኑ የፕላንና ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ባህሩ በበኩላቸው የተነሱ ችግሮች መኖራቸውን አምነው በቀጣይ ችግሮቹን ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በጥንካሬ የተወሰዱትንም በማስቀጠል ባለስልጣኑ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።