ሁለቱ ሚያዝያ 27ቶች- የድል ንሳት ቀናት! - ኢዜአ አማርኛ
ሁለቱ ሚያዝያ 27ቶች- የድል ንሳት ቀናት!

መንደርደሪያ...
ሚያዝያ 27 ገና ነው። ከሚያዝያ 27 በፊት የህዳር 27 ዋዜማ ዕለት 1927 ፋሺስት ጣልያን ላይ የአድዋን ቂም ወልውላ ወልወል(ኦጋዴን) ላይ ፀብ ክብሪት ጫረች። እሳቱን ጭራ ኢትዮጵያን ከሰሰች። የአገር ዘበኞች በፊታውራሪ አለማየሁ ጎሹ መሪነት ሰማዕትነትን ባረኩት። በዓመቱ ጥቅምት 23 ቀን 1928 ቀኝዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት (በኋላ ደጃዝማች) ቆራሄ ላይ ቆስለውም ከጠላት ጋር ተናንቀው መሰዋዕቱን ደገሙት። ወንድማማቾች ፊታውራሪ ጓንጉል ኮላሴና አቶ ኃይለማርያም ኮላሴም ጠላትን ሲያስጨንቁ ቆይተው ኃይለማርያም ሲሰዉ፤ ጓንጉል ኮላሴ ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል። ከወልወል ግጭት አሃዱ ያለችው ጣሊያን ወረራዋን ከአሥመራና ከሶማሊያ በሁሉም አቅጣጫዎች ወደ መሃል ኢትዮጵያ ቀጠለች።
የፋሽስትን ወረራ የተገነዘበችው ኢትዮጵያም መስከርም 22 ቀን 1928 ክተት አዋጅ አውጃለች። በአገር ዳር-ድንበር መደፈር የማይደራደረው አገሬው በክተት ዓዋጁ መሠረት አንካሴውን አሾለ፤ ጦርና ጎራዴውን ሳለ፤ ጥቅርሻ ያጠላበትን ጎራዴ አራገፈ፤ ዱላና ዘንጉን ነቀነቀ። በዘመኑ ጠመንጃ ያለው ለዛውም ኋላ ቀር የተባሉትን ናስማሰር፣ ስናድር፣ መስኮቭን ወለወለ። በዘመኑ ለኢትዮጵያ ብርቅ የሆኑት መውዜርና ለበንን ያለውም በኩራት ቃታ ሸቀሸቀ። ሌላው ግን 'ከጠላት ማርኬ ጠመንጃ እታጠቃለሁ' በሚል ተስፋ ጀሌውን ወደ ዘመቻ ገሰገሰ። ከዚሁ ጋር አንድ ታሪክ ማንሳት የአገሬውን ወጣት ወኔና ጦረኝነት ዶክተር ሀሮልድ ናስትሮይም የተባለ ሐኪም 'የተደበቀው ማስታወሻ' በሚል ባሳተመው መጻሕፍ ቀንጭቦ ማቅረብ ሁነቱን ይበልጥ ያስረዳል። በሽሬ ጦር ግንባር የዘመቱት ደጃዝማች አያሌው ብሩ ከሠራዊታቸው ውስጥ አንድ ሽመል የያዘ ታዳጊ ተመልክተው አስጠሩትና " በዚህ በሚያምር ዱላህ ምን ልታደርገበት ነው?" ሲሉት "ነጭ ልገድልበት ነው" ብሎ ይመልሳል። ደጃዝማቹ ተገርመው "እንደሱ ማድረግ አትችልም። በምትኩ ጠመንጃ ልስጥህ" አሉት። ወጣቱ ልጅ ግን "የለም! አመሰግናለሁ። ለአባቴ የማልኩለትን ቃል በኋል ጣልያን ገድዬ ጠመንጃውን ወስጀ አሳየዋለሁ። አለበለዚያ በዚህ የጦር ሜዳ እቀራለሁ" በማለት እምቢተኝነቱን አሳይቷል። እናም በማይጨው፣ ተንቤን፣ አምባራዶም፣ በሽሬ ጦር ግንባሮች የኢትዮጵያ ሰራዊት አድዋ ድልን ለመድገም ወደ ትግራይ ተራሮች አቀና። በደቡብና ምሥራቅ ኢትዮጵም በተመሳሳይ በተጠንቀቅ ፋሽስትን ወረራ ለመመከት ተጠናከረ።
ጣልያን ወደ ኢትዮጵያ ስትገባ የነበራት አቅምና የኢትዮጵያ አቅም ልዩነቱ የሰማይና ምድር ያህል የራቀ ነው። 782 ሺህ 390 ጠብመንጃ፣ መትረየስ 23 ሺህ 251፣ ታንክና መኪና 25 ሺህ 980፣ ጥይት ከ1 ሚሊዮን 890 ሺህ በላይ፣ 2 ሺህ 600 መድፍ፣ 500 አውሮፕላን፣ የጭነት እንስሳት 162 ሺህ 790፣ 7 ሚሊዮን 800 ሺህ የመድፍ ጥይት፣ 8 ሺህ የሆስፒታል መርከቦች፣ ቁጥሩ ያልታወቀ የእጅና የአውሮፕላን ቦምብና መርዝ ይዛለች። በሰው ኃይል ረገድም 25 ሺህ የጦር መኮንኖች፣ 509 ሺህ 700 እግረኛ ወታደሮች፣ 50 ሺህ የመንገድ ሠራተኞች፣ 12 ሺህ መምህራን፣ 3 ሺህ ጋዜጠኞችና ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰላዮች አሰማራች። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ወገን የጦር ሠራዊቱ ቁጥር ጀሌውን ጨምሮ 700 ሺህ ቢገመትም፤ ልብስ የለበሰና መሣሪያ የታጠቀ ግን 25 ሺህ ብቻ ሲሆን፣ 200 መድፍ፣ 50 ፀረ አውሮፕላን፣ 3 ሺህ 500 መትረየስ፣ 15 ትናንሽ አውሮፕላኖች ብቻ ይገመታል። ከውጭ ተገዝተው ጅቡቲ የደረሱ ጦር መሣሪያዎችና ጥይትም በኃያላኑ ሴራ ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ ተደረገ። ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የሰለጠኑ ወጣት ጦር መኮንኖችም አዲስ አበባን ብቻ እንዲጠብቁ ተወሰነ።
በዚህም ወደ ጦር ሜዳ የዘመተው ሠራዊት በመጀመሪያው ቀናት ጀብድ ሰራ። በበርካታ ዐውደ ውጊያዎች ድልን አጣጣመ። በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ጥቃት ቢደርስበትም፤ጠላትን ከማስጨነቅ አልተቆጠበም። በጦርነቱ ወቅት የግል ቂምና ጥላቻ ከአገር ፍቅር መብለጡ የተረጋገጠበት ጊዜ ነው። በሴራቸው የተታሙት፣ ለዙፋን የማይደራደሩት፣ ለክብርና አጀብ ተጨናቂው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከልጅ ኢያሱ እስከ ንግስተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት በኋላም ከንግስናቸው በኋላ ከበርካታ መኳንንት ጋር ተጋጭተዋል፤ ጦር ተማዘዋል። ንጉሡ ከማይጨው ግንባር ሽንፈታቸው በኋላ ወደ አውሮፓ በመሰደዳቸው (ለሊግ ኦፍ ኔሽ አቤቱታ ነው ተብሎ ቢታመንም) ከበርካታ መኳንንት ዘንድ ቅሬታ ውስጥ እንዳስገባቸውም ይታወቃል። ፋሽስት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር የተኳረፉ በርካቶቹ በንጉሱ ቢበደሉ፣ ቢከፉና ቂም ቢቋጥሩም ቅሉ፤ በአገራቸው ያልጨከኑ የክፉ ቀን ልጆቿ በርካቶች ናቸው። ቆፍጣናው መኳንንት ደጃዝማች በየነ ወንድማገኝ(ሊጋባው በየነ) ቅድመ ወረራ በንጉሠ ነገሥቱ ከግርፋት እስከ እስራትና ግዞት በደል ያስተናገዱ ቢሆንም፤ ጠላት የኢትዮጵያን ደጃፍ በወረረ ጊዜ ግን ጠመንጃቸውን ወልውለው በተንቤን ጦር ግንባር ተሰለፉ። አንዳንድ አዝማቾች ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቢመለሱም ኩሩው መኳንንት ግን 'ጠላት ከፊቴ ተቀምጦ እንዴት እመለሳለሁ' በማለት ከጠላት ፊት ለፊት በተንቤን ግንባር ግንባራቸውን ለአረር ሰጥተው ተሰውተዋል። ገና ከጅምሩ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ያልተጣጣሙት የአድዋው የጦር ገበሬ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በጠላት ወረራ ጊዜ እድሜያቸው ቢጃጅም፤ ወኔያቸው ትኩስ ነበርና በ80 ዓመታቸው አዲስ አበባን ከጠላት ጉሮሮ ለመንጠቅ ጦር አዝምተው መስዋዕትነት ከፍለዋል።
ልጅ ኢያሱን ከዙፋን በማውረድ ጀምሮ የቅርብ ዘመዳቸውን ራስ ጉግሳ ወሌን እስከ መውጋት ደርሰው ራስ ተፈሪን ወደ ንጉሠ ነገሥትነት እንዲመጡ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ደጃዝማች አያሌው ብሩ ኃይለ ሥላሴ ከነገሡ በኋላ 'ራስ' ተሰኝተው የበጌምድር ገዥ ለመሆን ሲጠባበቁ ተስፋቸው ከንቱ ሆነ። የበጌምድር ህዝብም 'አያሌው ሞኙ ሸዋ አማኙ፤ አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ' በማለት ዘፈነ። ጠላት በመጣ ጊዜ ግን ለጣልያን ይገባሉ ተብለው የተሰጉት ደጃዝማች አያሌው 10 ሺህ ጦር ይዘው በሽሬ ግንባር ጠላትን አስጨንቀዋል- በንጉሡ ጥርጣሬ ውስጥ ሆነውም።
በሁሉም ጦር ግንባሮች አስደናቂ ድሎችን ማጣጣም የጀመረው የወገን ጦር ግን በዘላቂነት ድል መንሳት አልቻለም ነበር። ይህም በምድር ላይ ማሸነፍ የተሳናት ፋሽስት ከ40 ዓመታት በኋላ ተዘጋጅታ በመጣችበት ጅምላ ጨራሽ መርዝ ጋዝና የአውሮፕላን ቦምብ ከሠራዊቱ ባሻገር በንጹሃን ላይ መርጨት ጀመረች። በዚህም ተዋጊ አውሮፕላን አይቶ የማያውቀው አገሬው ሠራዊት ክፉኛ ተጎዳ። እንዲህም ብሎ ተቀኘ፦
በትግራይ ቢመጣ መች ይገባ ነበር
በጎንደር ቢመነጣ መች ይገባ ነበር
በጎጃም ቢገባ መች ይገባ ነበር
በሸዋ ቢመጣ መች ይገባ ነበር
በሰማይ መጣ እንጂ በማናውቀው አገር... በማለት።
ጣልያን በዓለም ላይ የተከለከለ መርዝ ተጠቅማ ጅምላ ጭፍጨፋ አካሂደላች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞሶሎኒም ካለ ምንም ርህራሄና ምህረት የታላቋን የጣልያንን ጦር የሚተናኮሉ ሁሉ ፍጇቸው ብለው አዋጅ አውጥተዋል። ከ40 ሺህ በላይ ጦር የጎጃም ጦር ያዘመቱት፣ ከ10 ሺህ በላይ የደጃች አያሌውን የበጌምድር ጦር በማስተባበር በሽሬ ግንባር ከተሰላፉት ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ጋር የነበሩት፣ በኋላም ከጎሬ እስከ ጣልያን አገር ግዞት ከራስ እምሩ ጋር የተወሰዱት አርበኛው ደራሲና ዲፕሎማት ሀዲስ አለማየሁም በነበረው ጦርነት 'ትዝታ' በተሰኘው ማስታወሻቸው መዝግበዋል። “በውነት እንዲያ ያለውን መሣሪያ ምንም ጠላት ቢሆን በሰው ላይ ለማዋል የሚጨክን ሰው በልብ ፈንታ ሰብዓዊ ስሜት የሌለው ዐለት ድንጋይ የተፈጠረበት መሆን አለበት፤ እንዲያ ያለውን መሳሪያ በሰው ላይ ማዋል ሰብዓዊ ህሊና ሊሸከመው የማይችል እጅግ ከባድ መሆኑን አለም ሁሉ ያወቀውና ያወገዘው በመሆኑ የጣልያን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከማድረጉ በቀር ‘ሌላ መንግሥት በሌላ አገር አደረገ’ ሲባል ተሰምቶ የሚያውቅ አይመስለኝም..." ብለዋል። ተከዜ ላይ የሆነውን አሰቃቂ ሁነት ሲገልጹም "የተከዜ ውሃ እመሻገሪያው ላይ ሰፊና ፀጥ ያለ ነው። ታዲያ ያ ሰፊ ውሃ ገና ከሩቅ ሲያዩት ቀይ ቀለም በከባዱ የተበጠበጠበት ይመስላል። … መሻገሪያው በቁሙም በወርዱም ከዳር እስከ ዳር ሬሳ ሞልቶበት የዚያ ሬሳ ደምና ፈርስ ነው! የሰው ሬሳ የፈረስና የበቅሎ ሬሳ ያህያ ሬሳ ያውሬ ሬሳ ሬሳ ሬሳ ሬሳ ብቻ! እግር ከራስ ራስ ከግር እየተመሰቃቀለ እየተደራረበ ሞልቶበት፤ የዚያ ሁሉ ሬሳ ደምና ፈርስ ነው።… ያ የሬሳ ክምር… ከጦርነቱ ግንባር ሽሽት ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ መሰንበቻውን ሰውና ከብቱ ሊሻገር ሲገባ፤ አውሬ ውሃ ሊጠጣ ወይም ሬሳ ሊበላ ሲመጣ ሁሉም ባንድ ላይ እዚያ በቦምብ ሲያልቅ የሰነበተ መሆን አለበት።…” በማለት አስፍረዋል።
ሌላው ከላይ የጠቀስኩት የውጭ አገር ጸሐፊ ደግሞ ስለአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት የተመለከቱትን ትዝታ እንዲህ ይናገራል። "አንዲት ቆንጆ ሴት ድንጋይ ተደግፋ ተቀምጣለች። ከድህ ቤተሰብ መሆኗ ያስታውቃል። እንደ አመድ የገረጣው ፊቷና የጎደጎዱ ዓይኖቿ ያሳለፈቻቸውን መከራ ያስታውቃል። ምን ሆነሽ ነው ተብላ ስትጠየቅ ቀሚሷን ነበር ገልጣ የምታሳየው። ግራ እግሯ ከጉልበቷ በታች ተገንጥሎ የለም። ደም እንዳይፈስ በመቀነት ጥብቅ ብሎ ታስሯል።ጓደኞቿ የሉም። ምናልባትም ሞተውባት ይሆናል። በአባቷ አስከሬን አጠገብ ተቀምጣ ታነባለች..." በማለት አሰቃቂነቱን ይናገራሉ።
በመጨረሻም ህዝብ እንደቅጠል ረግፎ፣ እንስሳት ረግፈው ጦሩ ተፈታ። ንጉሠ ነገ
ሥቱም አገር ለቀዋል። የንጉሡ እንደራሴ ራስ እምሩ ቀሪው ጦር ይዘው ከኤርትራ ተወላጁ ኮለኔል በላይ ሃይላብ ከሚመራው የሆለታ ገነት ወጣት ጦር መኮንኖች ጋር ማዕከላቸውን ከአዲስ አበባ ወደ ጎሬ በማድረግ 'ጥቁር አንበሳ'ን ጦር አቋቁመው ለመታገል ሞከሩ። በመጨረሻም በአካባቢው ህዝብ ድጋፍ እጦትና በተደራጀ ጦር አመራር ችግር ተማርከው ጦሩም ተፈታ፤ ራስ እምሩና ሌሎች ጦር አዛዦችም ወደ ሮም ግዞት ተላኩ። የማዕከላዊ መንግስት ጦር ቢፈታም ዳሩ ከጦር ግንባሮች የተመለሰው ሠራዊትና በየአካባበው የሸፈተው አገሬው ሁሉ 'እምቢ ላገሬ' ብሎ ወደ አርበኝነቱ ገባ። በብዙ ፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ለማግኘት የሞከረው የሞሶሎኒ ጦር በህዝብ ላይ ባደረሰው ግፍና መከራ ኢትዮጵያውያንን ለዱር፣ ለገደል፣ ለሸንተረሩ እንጂ፤ ለሮም መንግስት ሊንበረከክ አልቻለም። ከከተማ እስከ ገጠር በጅምላ አውሮፕላን ቢጨፈጭፍ፣ ቤት ንብረት ቢያቃጥል ኢትዮጵያን እንዳሰበው የሮም ንጉሥ ግዛት አደርጎ መግዛት ግን ተሳነው። እናም ለቀጣይ አምስት ዓመታት ከ1928 አስከ 1933 ንጉሧ የኮበለለባትን አገር ላለማስደፈር አርበኞች በየፊናው ጉሮ ለጉሮ ሲተናነቁ ከረሙ። ጳውሎስ ኞኞ ''የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት'' በተሰኘው መጽሐፉ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በኋላ ካሳ ስትጠይቅ ያቀረበችው የጉዳት ወይም የኪሳራ ዝርዝር ውስጥ እንደተመለከተው በጦርነት 275 ሺህ ወታደሮች፣ 78 ሺህ 500 አርበኞች፣ 17 ሺህ 800 ሴቶችና ህጻናት ተገድለዋል።
በፋሸስት ተማርከው 24 ሺህ አርበኞች፣ የካቲት 12 ቀን በነበረው ጭፍጨፋ 30 ሺህ አዲስ አበቤዎች፣ በእስር ቤት 35 ሺህ ሰዎች፣ በስደትና ረሃብ 300 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል። 52 ሺህ ቤቶች፣ 2 ሺህ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። እምስት ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች፣ 7 ሚሊዮን በጎችና ፍየሎች፣ አንድ ሚሊዮን ፈረስና በቅሎዎች፣ 700 ሺህ ግመሎች ሞተዋል። ይህ መረጃ 'ኢትዮጵያ ከድል በኋላ ደርሶብኛል፤ ካሳ ያስፈልገኛል' ብላ ያቀረበችው መረጃ ነው።
በዚህ የአምስት ዓመታት ታሪክ ግን በጉልህ የሚጠቀስ አንድ ቀን አለ-አንድም የድል መንሳት፣ አንድም የድል መነሳት ዕለት-ሚያዝያ 27።
ሚያዝያ 27 የድል መንሳትና ድል መነሳት ቀን
ከአድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ በማርሻል ባዶሊዮ ፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ሚያዝያ 27 ቀን 1928 አዲስ አበባን ያዘ። የኢትዮጵያ ድል ጳውሎስ ኞኞ እንደሚለው "ሚያዝያ 27 ቀን ከሰዓት በኋላ ብረት ለበስ የሆነው የማርሻል ባዶሊዮ ጦር አዲስ አበባ ጫፍ ደረሰ። በአዲስ አበባ ኃይለኛ ዝናብ ይዘንባል። ነጎድጓዱ አዲስ አበባንን መድፍ የሚተኮስባት የጦር ሜዳ አስመስሏታል።... ማርሻል ባዶሊዮ በደመቀ አጀብ ታጅቧል። በፈረስ ተቀምጠው ዙሪያውን ካጀቡት መሃል በኋላ የአዲስ አበባ ገዥ የሆነው ጁሴ ቦታይ፣ የቅኝ ግዛት ዋና ፀሐፊ የነበረው የማርሻል አሌሳንድር ሌሴኖና ሌ የጣልያን ሹማምንት ነበሩ.... ጄኔራሎች እርስ በርሳቸው ይጫወቱ ነበር። ማርሻል ባዶሊዮ 'አደረግነው አደረግነው፤ ደህና ሁን አንተ የተከበርክ ጦርነት' አለ።
በተመሳሳይ 'ማርሻል ባዶሊዮ አዲስ አበባን ያዘ' የሚለውን ዜና የሮማ ህዝብ ሲሰማ ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ጎዳ ወጣ። ፒያዛ ቬኔዚያ የተባለው የሞሶሎሚ የዲስኩር መናገሪያ አደባባይ በሰው ተሞላ። ሞሶሎኒም ባልኮኒው ላይ ቆሞ 'ባለፈው የ3 ሺህ ዓመት ታሪካችን ውስጥ ኢጣሊያ አኩሪ ታሪካዊ ስራዎች ሰርታለች። ይህ የዛሬው ግን ምንም የማያጠያይቅ ከሁሉም የበለጠ ታሪካዊ ተግባር ነው'። የኢጣሊያ ህዝብ ሆይ፣ የዓለም ህዝብ ሆይ የሰላም መሠረት ዛሬ ተጣለ..." በማለት የእብሪት ንግግር አደረገ። የፋሺስቱ አለቃ ሞሶሎኒ ይህን ይበል እንጂ፤ ዳሩ የሰላም መሰረት አልተጣለም። ጣልያን በታሪኳ 'ማስተርድ ጋዝ' በተባለ መርዝ የሰው ልጆቿን የጨፈጨፈችበት አሳፋሪ ታሪኳ ነበር፣ ኢትዮጵያንን በቁጭት ወደ ዱር ገደሉ ዘልቀው አርበኝነት የጀመሩበትም ጊዜ ነበር። ያም ሆኖ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ለፋሺስት ጣልያን የድል ቀን ነበር። ኢትዮጵያ ደግሞ ድል የተነሳችበት ዕለት ሊባል ይችላል።
ታሪክ ግን ራሱን ደግሟል። ልክ በአምስት ዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 በአገረ እንግሊዝ-ግብጽ- ሱዳን አደርገው በጎጃም በኩል ተመልሰው አዲስ አበባን የገቡበት ዕለት ነበር። በእንግሊዞች የሚመራው ጦር ከአንድ ወር በፊት መጋቢት 28 ቀን አዲስ አበባ ቢገባም፤ ንጉሠ ነግሥቱ ግን ልክ በዛሬው ዕለት ነበር።ከአምስት ዓመት በፊት ከተለዩት ቤተ መንግሥት የገቡት፤ በታላቁ የምኒልክ ቤተ መንግ
ሥት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሸበረቀ የአገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ በክብር ያሰቀሉት።
ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ''ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ'' በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ፍቼ ሰንብተው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 እንጦጦ የደረሱት በማለዳው ነበር። "ሕዝቡን ለኛ ያለውን ፍቅር የገለጸበት ሁኔታ ባየን ጊዜ እንባችንን መቆጣጠር አልቻልንም፤ ስሜታችንም ጥልቅ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው የአምላክ ቃል አይታሰርም። ህዝቡ ለነጻነቱና ለብሔራዊ ሉዓላዊነቱ ያደረገው ተጋድሎ በበስደትም በእስር ቤትም የነበረው ሁሉ በዙሪያችን ከበበን። እንጦጦ ማርያም ከነበረው አቀባበል በኋላ ወደ ከተማችን በአርበኞች ግራ ቀኝ ታጅበን ወረድን። ...ቀጥሎ በፈረሰኛ ክብር ዘበኞች ታጅበን በክፍል አውቶሞቢል ተቀምጠን ታየን። 100 ሺህ የሚገመት ህዝብ በአዲስ አበባ ህዝብ እኛን ለመቀበል ለጠላት አጅ ሳይሰጡ ለአገራቸው ፍቅር ሲዋደቁ ለ5 ዓመት ጠላትን ሲያሸብሩ በነበሩ አርበኞች ትዕዛዝና ስርዓት አስከባሪነት አደባባይ ወጥቷል። ጎዳናዎች በአበባና በሠንደቃላማ ደምቀዋል። ህዝቡ እኛን ለመቀበል ከነበረው ጥልቅ ጉጉት የተነሳ መሬቱን እየሳመ፣ በደስታና ኅዘን ሲቃ የተቀላቀለበት እንባ እያነባ ነበር። በትርዒቱ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ፎቶ አንሺዎች ሂደቱን እየዘገቡና ታሪካዊ ሁነቱን እየመዘገቡ ነበር። በዚህ ሁኔታ በክብር ታጅበን እኩለ ቀን ላይ ታላቁ ቤተ መንግሥት ገባን። ቤተ መንግሥቱ ደጃፍ የእንግሊዝ ክብር ዘበኞች ግራ ቀኝ ቆመዋል።... ነጋሪት ተጎሰመ። የቀድሞው የእንግሊዝ ምስራቅ አፍሪካ ኮማንደር ሌፍተናንት ጄኔራል ካኒንግሃም በትልቅ ክብር ተቀበሉን ..." ሲሉ ይተርካሉ። (በቀጣዩ ቀን ሚያዝያ 28 ለአዲስ አበባ ህዝብ ረጅም ንግግር አድርገዋል)። ይህም የሆነው የዛሬ 79 ዓመት ልክ ዕኩለ ቀን ላይ ነበር። ሁነቱም ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ፋሺስት አዲስ አበባን መቆጣጠሩ ሮም በተሰማ ጊዜ እንደነበረው የደስታ ቅጽበት ይመሳሰላል። ዕለቱም የኢትዮጵያ አርበኞች ለአምስት ዓመታት ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ለአገራቸው ለተዋደቁላት፣ ለተሰውላት፣ ለታረዙላት፣ ለተቆሱላላት፣ ለነጻነቷ ለደሙላት ያልተከፈለ ውለታቸው መታሰቢያ ቀን እንዲሆን ተደርጓል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአዲስ አበባ በዓሉን ማክበር ባይቻልም፤ አርበኞች ለአገር የተከፈሉት ዋጋ በምንም የማይተመን፣ በየዓመቱም ትውልድ ሊዘክረው የሚገባው የታሪካችን አካል፤ ታሪካዊ ቀን ነው።