ቀጥታ፡

ከአባቶቻችን ፅናትና አንድነት በመማር ችግሮቻችን መፍታት እንችላለን -አርበኞች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2012 (ኢዜአ) ከቀደምት አባቶቻችን ፅናትና አንድነት በመማር በዘመኑ ያጋጠሙን ችግሮች መፍታት እንችላለን ሲሉ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አርበኞች የጣልያንን ወራሪ ኃይል ያሸነፉበት 79ኛው የድል በዓል ዛሬ  ታስቦ ውሏል።

በዓሉ የኢትዮጵያ አርበኞች ለአገር ነጻነት፣ አንድነትና ክብር ከሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች በመጉረፍ ድል የነሱበት መሆኑም ይታወቃል።

አርበኞቹ ለአምስት ዓመታት ባደረጉት ተጋድሎ ያንበረከኩበት፣አልበገር ባይነታቸውን በማስመስከር ድል የተቀዳጁበት እንደሆነም የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ።

በዓሉ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ስጋት በሆነው ኮቪድ-19 ምክንያት አባት አርበኞች በፉከራ፣ በሽለላ፣ በቀረርቶና ሌሎችም ትርኢቶች ታጅቦ በአደባባይ አልተከበረም።

ሕዝቡም ወረርሽኙን ተከትሎ በወጣ አስቸኳይ ዓዋጅ  መሠረት በብዛት ወጥቶ ሊያከብረው አልቻለም።

በዚህም መንግሥት በደነገገው መሠረት ጥቂት ጀግኖች አርበኞች በተገኙበት በዓሉ አዲስ አበባ በሚገኘው የድል ሐውልት ታስቦ ውሏል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ጀግኖች አርበኞች እንዳሉት ቀደምት አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ነፃነቷና ሉአላዊነቷ ያስረከቧትን አገር ትውልዱ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊያስቀጥል ይገባዋል። 

የአርበኛ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሌ እናትና አባት አርበኞች የዘር፣ የሃይማኖት፣ የጎሳ፣ የቀለም ና የአስተሳሰብ ልዩነቶች ሳያግዷቸው ጠላትን ድል ማድረግን ትውልዱ መማር አለበት ብለዋል።

በመሆኑም የእነርሱን ጽናትና ችግርን በጋራ የመጋፈጥና የማለፍ ባህል ተላብሶ መትጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የሥራ አመራር አርበኛ ዳኛቸው ተመስገን የአባቶችን ጽናትና ጥንካሬ በመውረስ የጊዜውን ፈተና ማለፍ ይቻላል ይላሉ።

በትዕግስት ሆኖ ከመንግሥት የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበር ወረርሽኙንም ድህነትንም ታሪክ ማድረግ ይቻላልም ብለዋል።   

የበዓሉ አስተባባሪ አቶ ተሾመ አየለ በበኩሉ አሁን ዓለም የገጠማት ፈተና ዘር፣ ሃይማኖትና ቀለም የማይለይ አስከፊ ወረርሽኝ ነው ይላል።

ጀግንነት ማለት ኅብረት፣ መደማመጥ በመሆኑ ይህንን የገጠመውን ችግር ለማለፍ መደማመጥና መመመሪያዎችን በሥራ በመተርጎም ማለፍ እንደሚቻል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም