ቀጥታ፡

ማህበሩ የኮቪድ-19 ለመከላከል 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ለተቋማት ማስረከብ ጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26 /2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር የኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚያስችሉ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ቁሳቁስ ለሕክምና ተቋማት ማስረከብ ጀመረ።

ማህበሩ ለተቋማቱ ማስረከብ የጀመረው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት ባገኘው ገንዘብ የገዛቸውን የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ነው።

ማህበሩ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚድዋይፎች ቀንን ምክንያት በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል ድጋፉን በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ማስረከብ ጀምሯል።

የማህበሩ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ የሺጥላ ተስፋዬ እንደገለጹት ማህበሩ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነውን ኮሮና ለመከላከል አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

በዚህም በተለይ በእናቶችና ህጻናት ዙሪያ ለሚሰሩ የጤና ተቋማት ድጋፉን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ድጋፉም የፊት ጭምብል፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣ ለህክምና ባለሙያዎችና በሆስፒታሉ ለሚገኙ እናቶችና ህጻናት የሚሆኑ አልባሳት እንዳካተተ አስታውቀዋል።  

በቀጣይም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ቁሳቁስ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱም ከተማ መስተዳድሮች ለሚገኙ የህክምና ተቋማት እንደሚያበርክት አቶ የሺጥላ ተናግረዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም ማህበሩ ላደረው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የእናቶችና ህጻናት ህክምና ትኩረት እንደሚሻ  ገልጸው፤ በኮቪድ 19 ምክንያት የወሊድ፣ የቤተሰብ እቅድና የጨቅላ ህጻናት ሌሎች የጤና አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በማምራት በወሊድ ወቅት የሚገጥማቸውን ችግር መቀነስ እንዲሁም ከቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ጋር በተገናኘም ላልተፈለገ እርግዝና ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ሁሉም መሰረታዊ አገልግሎት ሳይስተጓጎሉ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰጡ ድጋፍ በማድረግ እንዲያደርግም ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም