ቀጥታ፡

በከተሞቹ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በሐረርና በድሬዳዋ ከተሞች ባለፈው ቅዳሜ በተደረገ ክትትል 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽነር አስታወቁ። በክትትሉ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ፣ ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ መድኃኒትና የምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ክትትሉን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በከተሞቹ በተካሄደው ቁጥጥር በሕገወጥ መንገድ የገቡት ዕቃዎች ተይዘዋል።

በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴ ዕቃዎቹ በስድስት መጋዘኖች ተከማችተው መያዛቸውን አስታውቀዋል።

ከዕቃዎቹ መድኃኒት፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችና ቅባቶች ይገኙበታል ብለዋል።   

በክትትሉ ሂደት በኮንትሮባንዲስቶችና በተባባሪዎቻቸው እንዲሁም በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉንና ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

የፀጥታ አካሉ ግጭቱን እያጣራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኮንትሮባንዲስቶቹ በጦር መሣሪያ ታግዘው ንብረታቸውን ለማስለቀቅ ቢሞክሩም፤ ከነግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በክትትሉ ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የፌዴራል፣ የሐረሪ ክልልና የድሬዳዋ ፖሊስና ልዩ ኃይል እንዲሁም የኢትዮጵያ መድኃኒትና የምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሔራን ገርባ በበኩላቸው ክትትሉ የተደረገው በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል እየተስፋፋ የመጣውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ለሦስት ወራት ጥናት ከተደረገ በኋላ ነው ብለዋል።

በዚህም በድሬዳዋ ከተማ 12 ሚሊዮን ብር፡ በሐረር ደግሞ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ዕቃዎች መያዛቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢዎቹ የሚደረገው ክትትል እንደሚጠናከርም ወይዘሪት ሄራን አስታውቀዋል።


በክትትሉ ሕይወታቸውን ላጡትና ለቆሰሉ ወገኖች ኅዘናቸውን ገልጸዋል።  


በአገሪቱ በተያዘው ወር ብቻ 120 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት ይገልጻል።


በአገሪቱ የአዳንዛዥ ዕጽ፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ምግብ ነክ ዕቃዎች ኮንትሮባንድ እየተስፋፋ መምጣቱን በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም