ቀጥታ፡

መንግስት ኮቪድ 19 ለመከላከል ለልማት አጋሮች ያቀረበው ጥያቄ በጎ ምላሽ እያገኘ ነው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያስገትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቀነስ ለልማት አጋሮች ያቀረበው የድጋፍ ጥያቄ በጎ ምላሽ እያገኘ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ዓለም አቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ በተለይ በታዳጊ አገሮች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

አገራቱ ለልማት ያውሉት የነበረውን በጀት ጭምር ወረርሽኙ በዜጎቻቸው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለሰብዓዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲያውሉም ተገደዋል።

ኢትዮጵያም ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ለሰብዓዊ ምላሾች የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋታል ብለዋል ዶክተር እዮብ።

ባለፈው ሳምንት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ስራስፈፃሚ ቦርድ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት ለማገዝ 411 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።''

አበዳሪ አገሮች ለኢትዮያ ተጨማሪ ብድር የመስጠት ፍላጎት ማሳየታቸውንና ከዚህም ባለፈ ቀደም ሲል አገሪቷ ተበድራ የነበረውን ብድር የመክፈያ ጊዜ ለማራዘም ፍቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውን ዶክተር እዮብ ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በኒውዮርክ ታይምስ መፅሄት ላይ ባወጡት ፅሁፍ ‘’አበዳሪ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አዳጊ አገራትን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ የከፋ ተፅዕኖ ለመታደግ የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘም ሳይሆን ብድርን መሰረዝ ይገባቸዋል’’ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቸኳይ የዕዳ ስረዛው በተለይም በአፍሪካ ከኮቪደ-19 ጋር ተያይዞ እየከፋ ለመጣው የምግብ ዋስትና ችግር አስፈላጊ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የቡድን 20 አባል አገራት እኤአ በሚያዚያ 5 ቀን 2020 ለታዳጊ አገራት የዕዳ መክፈያ ጊዜ እስከ ዓመቱ መጨረሻ እንዲራዘም መወሰናቸው ይታወሳል።

የአገራቱ ውሳኔ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአፍሪካ አገሮች የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በተሻለ ሁኔታ ለመከላከል ያስችላል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ።

የቡድን 20 አገራት የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ብድሮች እፎይታ እስከ ዓመቱ መጨረሻ መስጠታቸው ለኢትዮጵያ ብቻ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ያስቀርላታል።

ይህ የእፎይታ ጊዜ እንደ አውሮፓውያኑ እስከ 2022 ከቆየ ደግሞ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ እንድታገኝ ያስችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም