ቀጥታ፡

የትምህርት ዘርፉ በሁለት ሚኒስቴር ከሚመራበት ደረጃ ደርሷል ተባለ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የትምህርት ዘርፉ በሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከሚመራበት ደረጃ ላይ መድረሱን የትምህርት ሚንስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ተናገሩ። የትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትምህርት ሚኒስቴር  የ2011 በጀት ዓመት ረቂቅ እቅድ፣ የ2010 በጀት ዓመት ክንውኖችና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል። በውይይቱ  ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንደተናገሩት "በአሁኑ ወቅት ያለው የትምህርት ሚኒስቴር አደረጃጀት የአገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ለደረሰበት ደረጃ ምላሽ ሰጪ አይደለም"። በአገሪቷ የትምህርት ተቋማት እየተስፋፉ በመምጣታቸው፣ ከትምህርት ዘርፉ ውስብስብነት፣ የትምህርት ስርዓቱ ከሚመራበትና በዝግጅት ላይ ካለው የ15 አመቱ ፍኖተ ካርታ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች አንጻር "ዘርፉ በአንድ ሚኒስቴር እየተመራ ሊቀጥል አይችልም" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት 50 ዩኒቨርስቲዎች፣ 30 ሚሊዮን ተማሪዎች፣ 40 ሺህ ትምህርት ቤቶች፣ ከ1 ሺህ 500 በላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትና የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአገሪቷ ይገኛሉ። ይህም ሚኒስቴሩ አሁን ባለው አደረጃጀትና የሰው ኃይል ተልዕኮውን የማስፈጸም ብቃትና አቅም እንደሌለውም አንስተዋል። የሚንስትር ዴኤታዎችንና የከፍተኛ አመራሮችን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚጠይቁ ስትራቴጂክ የሆኑ ስራዎች በባለሙያዎችና በዳይሬክተሮች ደረጃ እየተሰሩ ናቸውም ብለዋል። በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር አደረጃጀቱን በሁለት ሚኒስቴር መክፈል አስፈላጊ መሆኑንና ጥናት መደረጉንም ተናግረዋል ሚኒስትሩ። የትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ የአጠቃላይ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናና የከፍተኛ ትምህርት ዘርፎች ለየብቻ ራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ ሀሳብ አቅርበዋል። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር አገላለጽ ግን ዘርፉ በሁለት አደረጃጀት ተከፍሎ የአጠቃላይ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በአንድ ሚኒስቴር ሆነው የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ደግሞ ለብቻው በሚኒስቴር ደረጃ እንዲቋቋሙ የሚያስችል ረቂቅ መዘጋጀቱን ነው ያስታወቀው። ረቂቁ በቀጣዩ ሳምንት ለሚንስትሮች ምክር ቤት የሚቀርብ መሆኑን ገልጸው በሚኒስቴር ደረጃ የሚቋቋሙ ዘርፎችን የመለየት ስራው በሚንስትሮች ምክር ቤት የሚወሰን መሆኑም ተናግረዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ በሚኒስቴሩ የ2010 በጀት ዓመት አፈጻጸም ላይ የትምህርት ጥራት መጓደል፣ የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮች ድጋፍና ክትትል ማነስ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ማስፋፋት፣ ከመምህራን ብቃት ምዘና የአላፊዎቹ ምጣኔ ጋር የታዩ ክፍተቶችን አንስተዋል። በሚኒስቴሩ ስር ባሉ ተጠሪ ተቋማትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታዩ የሀብት አጠቃቀም ችግሮችና የኦዲት ግኝቶች እንዲሁም ከዩኒቨርስቲዎች የማስፋፊያ ግንባታዎችና ከሌሎችም ጉዳዮች አንጻር ያሉ ክፍተቶችና በቀጣዩ በጀት ዓመት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችንም ጠቃቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም