የሰው ዘር ቅሪተ አካል የተገኘበት ስፍራ ባለመልማቱ ቅሬታ አድሮብናል- የአካባቢው ነዋሪዎች

ሰመራ ሚያዝያ 30/2010 በአፋር ክልል የአደአር ወረዳ ሉሲን የመሳሰሉ የሰው ዘር ቅሪተ አካል መገኛ እንደሆነ ቢታወቅም ስፍራው ባለመልማቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው በአካባቢው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን  በበኩሉ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መዘጋጀቱን አመልክቷል። ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ፋጡማ ጉራ እንደተናገሩት አካባቢው ለሀገር ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ ያላቸውን ሉሲና ሰላም ጨምሮ  ቀደምት የሰው ዘር ቅሪተ አካል መገኛ ነው፡፡ ሆኖም አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ብሎም ህብረተቡን በተለይም ወጣቱን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራት እንደሌሉ አመልክተዋል፡፡ ስፍራው የመስህብ ስፍራና የገቢ ማስገኛ ሆኖ እንዲለማ ባለመደረጉ  ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ አሳሃመድ ሁመድ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው ከ1986 እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ በአካባባው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የተመራማሪ ቡድኖች ጋር በቁፋሮ ስራ በመሳተፍ የተለያዩ ቅርሶችን በማገኘት  ከተመራማሪዎቹ የምስክር ወረቀት መቀበላቸውን ተናግረዋል። ይሁንና ራሳቸውን ጨምሮ ለአካባቢዉ ነዋሪዎች  ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ የስራ እድልና የልማት አውታሮች ይዘረጋሉ ብለው በተስፋ ቢጠብቁም እስካሁን ያዩት ነገር እንደሌላ አስረድተዋል፡፡ " ሉሲ  ቀደምት የሰው ዘር ቅሪተ አካል መሆኗን  ያረጋገጠች፣  የዘርፉን ተማራማሪዎችንና ቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገች የሀገራችን አደአር  ግኝት ናት" ያሉት ደግሞ በወረዳው የማስታወቂያ ጽህፈት ቤት የቱሪዝም ልማት ባለሙያ  አቶ መሃመድ ኤሴ ናቸው፡፡ ወረዳው ከሉሲ በተጨማሪ አርዲ፤ ሰላምና ከዳባ የመሳሱ የቀደምት ሰው ዘር  ቅሪተ አካል  እንዲሁም ጥንታዊ የመገልገያ ቁሳቁሶች የተገኙበት ቦታ ቢሆንም ለአካባቢው አርብቶ አደር ህዝብ  ህይወት መለወጥ እስካሁን ያስገኙት ጥቅም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ ለአካባቢው የቅርስ መገኛ ስፍራ የነበረው የባለቤትነት ስሜት መቀነሱን አመልክተዋል። ስፍራው  ጥበቃና እንክብካቤ ስለማይደረግለትም  አካባቢው የቆሻሻ መጣያ ከመሆኑም በላይ ተሽከርካሪዎችም ጭምር እንደ መንገድ በመጠቀም  የቅርስ መገኛ  ቦታዎቹ  ደብዛቸው እየጠፋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ ያዮ ሉሲ በአለም አቀፍ ደረጃ   ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች አንዷና ቀዳሚ ብትሆንም ለመካነ ቅርሱ አካበቢ ተገቢው ጥበቃና እንክበካቤ አለመደረጉን ገልጸዋል። የአካባቢው ህብረተሰብም ከግኝቶቹ ተጠቃሚ እንዳልሆነ  ጠቁመው  ቢሮው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስለጣንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ ለችግር መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ቢጠይቁም መልስ አለማገኘታቸውን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የጥናትና ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የመካነ-ቅርስ አስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ጸሐይ እሸቴ የሉሲ መገኛ አካባቢን የማልማቱ ጉዳይ ለዩኒስኮ ብቻ የተጣለ ኃላፊነት አድርጎ የማየትና ባለድርሻ አካላት  በቅንጅት ያለመስራት ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በቅርሱ መገኛ አካባቢ እስካሁን ተገቢው ጥበቃ ካለመደረጉም በላይ  ህብረተሰብም የልማትና የሰራ እድል ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረጉን አውስተዋል። "በቅርቡ ከአውሮፖ ህብረት በተገኘ 400 ሺህ ዩሮ በኦሞ ሸለቆና በታችኛው አዋሽ ሸለቆ አካባቢ ለሚገኙ የሉሲና ሌሎች ቅሬተ አካል መገኛ ስፍራዎችን  የማልማት ቅደመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው " ብለዋል። በአደአር ወረዳም ለተመራማሪዎችና ጎብኚዎች መረጃ የሚሰጥ ማዕከል ግንባታ እንደሚከናወን ጠቁመው  እስከ 40 የሚሆኑ የአካባቢውን ወጣቶች ደግሞ  በእደ-ጥበብ ሙያ  በማሰልጠን  ወደስራ የሚገቡበት የመንቀሳቀሻ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል። የማዕከሉን ግንባታ ጨምሮ ወጣቶቹን አሰልጥኖ ወደስራ የማስገባቱ ስራ እስከ 2011ዓ.ም ታህሳስ ወር ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ቅርሶቹ  የተገኙበትን አካባቢም ከአደጋ ለመከላከል ቦታዎችን የመለየትና የማካለል ስራዎችን ከኢትዮጵያ ካርታ ሰራዎች አጄንሲ ጋር  እየሰሩ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም