ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በገጠር ወረዳዎች የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ቤቶችን የጸሐይ ኃይል ተጠቃሚ እያደረገ ነው

አርባ ምንጭ ሰኔ 27/2010 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ጎፋ ዞን የኤሌክትሪክ ኃይል በማይደርስባቸው የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ቤቶችን ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት  ዳይሬክተር ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ተቋሙ ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደርና በጀርመን አገር ከሚገኘው "ሳሃይ ሶላር አሶሴሽን" ጋር በመተባበር ጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በእዚህም ፕሮጀክቱ በ2002 ዓ.ም ከተጀመረ ወዲህ በስምንት ዓመታት ውስጥ 22 ጤና ጣቢያዎችንና 13 ትምህርት ቤቶች ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካክል ስድስት ጤና ጣቢያዎችና አራት ትምህርት ቤቶች እየተገባደደ ባለው የ2010 በጀት ዓመት ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው። የፀሐይ ኃይልን የሚሰበስበው መሳሪያ እያንዳንዱ ከ750 እስከ 1 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ዶክተር ተክሉ ገልጸው በተከናወኑ ሥራዎች 518 ሺህ 574 የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ዶክተር ተክሉ እንዳሉት ከጸሐይ ኃይል የሚገኘው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የገጠር ወረዳ ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አስችሏል፡፡ በጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዚጊቲ መጬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ተፈሪ ወጋየሁ በፕሮጀክቱ ትምህርት ቤቱ የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ተማሪዎች ትምህርት በሬዲዮ እንዲከታተሉ ከማስቻሉም በላይ በማታው ክፍለ ጊዜ ተግባር ተኮር ጎልማሶችን ለማስተማር እያገዛቸው መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም በፀሐይ ኃይሉ ለመምህራንና ለአካባቢው ነዋሪዎች በአነስተኛ ዋጋ የሞባይል ቻርጅ አገልግሎት በመስጠት ትምህርት ቤቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ24 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡ ጤና ጣቢያው የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚ በመሆኑ ክትባቶችንና መድኃኒቶችን በማቀዝቀዣ ውስጥ በማቆየት ደህንነታቸውን ለመጠበቅ አስችሏል" ያሉት ደግሞ በቦንኬ ወረዳ የዴንቢሌ ጤና ጣቢያ ባለሙያ ነርስ ሠራዊት ገቸረ ናቸው፡፡ " ከእዚህ በተጨማሪ የፀሐይ ኃይሉ ማታ ማታ ድንገት ለሚመጡና ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማን በአግባቡ አገልግሎት ለመስጠት አስችሎናል" ብለዋል፡፡ በዞኑ ካንባ ወረዳ የቦላንኮ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ከድር ካታላ በበኩላቸው ጤና ጣቢያው የፀሐይ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆኑ በፊት ሕሙማን የቤተሙከራ አገልግሎት ለማግኘት ብቻ 57 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ይሄዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ "በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በጤና ጣቢያው ማግኘታቸው የሕብረተሰቡን ጉልበት፣ ጊዜና ወጪ መታደግ ተችሏል" ብለዋል። በተጨማሪም የጸሐይ ኃይሉ በወሊድ ጊዜ ለእናቶች የተሻለ አገልግሎት ለመሰጠት የሚያስችል በመሆኑ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም