የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ ልዩ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ ልዩ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2012( ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው እለት በሚያካሂደው ሶስተኛ ልዩ ስብሰባው ምርጫን በተመለከተ በሚቀርቡ የመፍትሔ አማራጮች ላይ ተወያየቶ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባው ምርጫን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ ለህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል።
በእለቱ የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ሰፊ ክርክርና ውይይት በማድረግ በ3 ተቃውሞ፣ በ7 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ለቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ተደርጓል።
ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ በነገው እለት ሶስተኛ ልዩ ስብሰባውን በማድረግ ምርጫን በተመለከተ በሚቀርቡ የመፍትሔ አማራጮች ላይ የሚወያይ የሆናል።
በመሆኑም ምርጫን በተመለከተ ከቀረቡ አራት የመፍትሔ አማራጮች መካከል ቋሚ ኮሚቴው መርምሮ የሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም በስድስት የተለያዩ የብድር ስምምነቶች ላይ ውይይት በማድረግ እንደሚያጸድቅ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።