የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ይጀመራል
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ ከሐምሌ ስድስት ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ጉባኤው “በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝኃነት ሰብአዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት” በሚል መሪ ሐሳብ ከሐምሌ 10 እስከ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽና በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል። ከምስራቅ አፍሪካና ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተወጣጡ ከ300 በላይ ጳጳሳት፣ ካህናት፣የአጋር ድርጅቶች ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በውይይቱ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስታውቃለች። ጉባኤው ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለምታከናውናቸው ሃይማኖታዊ ማህበራዊ ስራዎች ብዝኃነትን ማስተናገድ እንዲቻል አቅጣጫ የሚቀመጥበትና ጳጳሳት ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የሚያስተላልፉበት እንደሆነ ተገልጿል። በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በግልፅ የሚዳስሱ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡም ታውቋል። በአጠቃላይ ጉባኤው በምስራቅ አፍሪካ አገሮች ጎልተው በሚታዩ የብዝኃነት ጸጋዎች ላይ የሚመክር እንደሆነ ቤተክርስቲያኒቷ አስታውቃለች። ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚሏቸዉን ጉዳዮች ለውይይት እንደሚያቀርቡና የመፍትሄ ሃሳቦችን እንደሚያካፍሉ ተጠቅሷል። ታህሳስ 14 ቀን 2010 ዓ. ም ለጉባኤው በአዲስ አበባ በተካሄደ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት መንግስት ለጉባኤው መሳካት ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ በጉባኤው ከብዝኃነት፣ እኩልነትና አንድነት አኳያ ተሞክሮዎችን የምታገኝበት እንዲሁም የእርሷን ለሌሎች የምታስተላልፍበት እንደሚሆንም ተናግረዋል። የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ከ56 ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን ጉባኤው በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ነው። አመሰያ ከአራት ዓመት በፊት በማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ ባካሄደው 18ኛው ጉባኤ፣ ኅብረቱን ለአራት ዓመታት ኢትዮጵያ በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ አማካኝነት በፕሬዚዳንትነት እንድትመራ መምረጡ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ የህብረቱ አባል አገሮች ሲሆኑ፤ጅቡቲና ሶማሊያ የህብረቱ ተባባሪ አባላት ናቸው።