ከፖለቲካ አጀንዳ ይልቅ ለሰው ህይወት ቅድሚያ መስጠት ይገባል … ምሁራን

ሚያዚያ 26/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ዘላቂ አንድነት ለማስቀጠል ከፖለቲካ አጀንዳ ይልቅ ለሰው ህይወት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የወሎና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ገለፁ።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

"አለም በኮሮና ቫይረስ እየተናወጠች ባለችበት ወቅት የፖለቲካ አጀንዳ ዋጋ የለውም" ያሉት ምሁሩ፤ ቅድሚያ ለሰው ህይወት መስጠት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

"በየትኛውም መመዘኛ አገርና ህዝብ ለአደጋ ተጋልጦ ባለበት በዚህ ወቅት ምርጫ መኖር አለበት ብሎ የሚያስገድድ ፖለቲካ ሊኖር አይገባም" ሲሉ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የምርጫ ወቅት ቢደርስም መራዘሙ አግባብና ተገቢ ነው ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽመልስ፤ ማንኛውም ጉዳይ የሚፈጸመው ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል ።

መንግስት የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አማራጮች ማቅረቡንም በማድነቅ፤ ከቀረቡት አማራጮችም አሁን ከገጠመን ችግርና አገራዊ ሁኔታ አንጻር ህገ መንግስት መተርጎም የተሻለ አማራጭ ሃሳብ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ህገ መንግስቱን ፈትሾ አወዛጋቢና ማብራሪያ ለሚሹ አንቀጾች ተገቢ ትርጉም በመስጠትና በማብራራት አገርን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤  ተፎካካሪ  የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራንም ከመንግስት ጎን በመቆም ማገዝና ሃሳብ መስጠት እንደሚገባቸው ምክር ለግሰዋል ።

"ይህን ክፉ ቀን ማለፍ የሚቻለው በመተባበር፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት ሀገራዊ ግዴታን በመወጣት እንጂ የሚሰሩ ሰዎችን ማደናቀፍ፣ሃሳባቸውን ማጥላላትና ስህተት መፈለግ ሊሆን አይገባም" ሲሉም አክለዋል ፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ተስፋዬ በበኩላቸው ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የህብረተሰቡን ደህንነት የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው ነው ያሉት ፡፡

ቫይረሱን ለመከላከል የምርጫው መራዘም ወሳኝ ቢሆንም በምን መልኩ የሚለውን ግን ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየትና የመፍትሄ አቅጣጫን በመግባባት ማስቀመጥ እንደሚገባም መክረዋል።

ከቀረቡት አማራጮችም ህገ መንግስት መተርጎም የተሻለ መሆኑን ጠቅሰው፤  ቅሬታ በማይፈጥር መልኩ ባለድርሻ አካላት ማወያየትና ማሳተፍ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ወረርሽኙ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚፈታተን በመሆኑ ሁሉም ተባብሮ አገርንና ህዝብን ማዳን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር አቶ አብነት እንዳሉት ደግሞ ምርጫውንም ሆነ ሌላው ተግባር ማካሔድ የሚቻለው "አገር ሰላም፤ ህዝብ ደግሞ ጤና ሲሆን ነው" በማለት ምርጫውን ለማራዘም የቀረበው ሓሳብ ከወቅቱ ጋር የሚሔድና ተቀባይነት ያለው ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም