የህብረተሰባችን መዘናጋት አሳሳቢና ለኮሮናቫይረስ መሰራጨት በር የሚከፍት ነው - አምባሳደር ተሾመ ቶጋ - ኢዜአ አማርኛ
የህብረተሰባችን መዘናጋት አሳሳቢና ለኮሮናቫይረስ መሰራጨት በር የሚከፍት ነው - አምባሳደር ተሾመ ቶጋ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2012 (ኢዜአ)``የህብረተሰባችን መዘናጋት አሳሳቢና ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መሰራጨት በር የሚከፍት ነው፤ ስለሆነም ህብረተሰቡ ለወረርሽኙ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል'' ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያለፈው ታህሳስ መጨረሻ አካባቢ ተከስቶ ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የሄደ በሽታ ነው።
ቫይረሱ በአለም የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈና ሚሊዮኖችንም ያጠቃ አሳዛኝ ክስተት ለመሆን መብቃቱን አምባሳደር ተሾመ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስታውሰዋል።
ቫይረሱ በቻይና ከሰማንያ ሺህ በላይ ሰዎችን ያጠቃና ከአራት ሺህ በላይ ህይወት የቀጠፈ ወረርሺኝ ነው።
በሕዝብ ዘንድ እንቅስቃሴ በመዝጋት የተለመደው ማህበራዊ ሕይወትን በመገደብ የሥነ ልቦና ጫና ፈጥሯል፡፡
በቻይና ጠንካራ የሆነ ዕለታዊ የምርመራ፣ የክትትልና የሪፖርት ሥርዓት በመዘርጋት እያንዳንዱን የበሽታውን ሥርጭት የተመለከቱ ጉዳዮች በሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲታወቁና አስፈላጊ እርምጃ በወቅቱ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡
የዜጎችና የተጓዦችን የጤና ሁኔታ ለማወቅ ሙቀታቸውን መለካት፣ ምርመራ ማድረግና ዜጎች ወደ ከተሞች በሚገቡና በሚወጡበት ወቅት የሚጠቀሙትን የጤና መግለጫ ካርድ መሰጠቱ በሽታውን በጊዜ ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል፡፡
በጠና ለታመሙ ሰዎች የጤና ክትትልና ህክምናን "አራት አካላትን ማቀናጀት" በሚል የታመሙ ሰዎችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ ሀብትንና ለኮሮናቫይረስ ብቻ የተለዩ ማዕከላትን በማቀናጀት መሥራት ከቻይና የሚወሰድ ተሞክሮ ነው ብለዋል።
ሁሉንም ከተሞችና ወረዳዎች ሆስፒታሎችን ለቫይረሱ ህክምና መስጠት በሚቻልበት ቁመና በመቀየር፣ የሆስፒታሎችን ቁጥር በመጨመር፣ የጤና ባለሙያዎችን በስፋት በማሰማራትና አማካሪዎች ምክር እንዲሰጡ በማድረግ በጠና የታመሙ ሰዎችን ከሞት ለማትረፍ ከቻይና ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ጠንካራ የበሽታ ሥርጭት ክትትል በታማሚዎችና በማህበረሰብ ደረጃ በመዘርጋት የቫይረሱን ምንጭ መለየትና የተነጣጠረ የመቆጣጠሪያ ስልቶችን ተፈጻሚ ማድረግ ስርጭቱን ለመከላከል አጋዥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው የስፖርት፣ ሲኒማ፣ ቲያትርና ሌሎች ሁነቶችን በማቋረጥ፣ የትምህርት ተቋማት ከአዲሱ ዓመት በኋላ የሚከፈቱባቸውን ጊዜያት በማራዘም ቻይና የወሰደችው ርምጃ ለኢትዮጵያ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
ትምህርት በበይነ-መረብ እንዲሰጥ መደረጉና ለሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮ ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶች ብቻ ክፍት እንዲሆኑ በማድረግ፤ የተለያዩ ተቋማት ሥራ የሚጀመሩባቸውን ጊዜያት በማስተካከል የወሰደችው እርምጃ ስርጭቱን ለመግታት አስችሏል።
የመድሃኒት አቅርቦትንና ዋጋ ማሻሻልና በበሽታው ለተጠቁ የራስ መጠበቂያ ቁሳቁሶችንና የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት እንዲሟሉ ሰርታለች።
የአስቸኳይ ጊዜ የቁሳቁስ ድጋፍን በተመለከተ የማምረት አቅም ግንባታ እንዲሰፋ በማድረግ፣ የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ ተቋማትን በማደራጀት፣ በየአካባቢው ያለ አስመጪ ድርጅቶችን በመደገፍና፣ የድንበር ዘለል የኤሌክትሮኒክስ ንግድ መሠረተ-ልማቶች በማቀናጀት የህክምና መሳሪያዎችን እንዲያስገቡ በማድረግ የአቅርቦት ሥርዓቱን በአስተማማኝነት አሻሽላለች።
የአደጋ ጊዜ ምላሽና የመከላከል ሥራዎችን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማሳተፍ ማከናወንና አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ህዝባዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ስርጭቱን ለመግታት መቻሏን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎችም ቻይና ሁሉንም የማህበረሰብ አካላት በሙሉ እንደ አንድ ማንቀሳቀስና ጠንካራ የፈጣን ምላሽ ሥርዓት መዘርጋት መቻሏ አዳዲስ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በስፋት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አምባሳደር ተሾመ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ከሌላው ዓለም አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ወደ ቻይና በመግባት ወረርሽኙ ድጋሚ እንዲይከሰት የሚያስችል ጥብቅ እርምጃዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የቻይና መንግሥት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በመመደብ ከፍተኛ የባለሙያ ንቅናቄ በመፍጠርና ቁሳቁስ በማሰባሰብ እንዲሁም የጤና መሰረተ ልማት በመገንባት፣ የጥናትና ምርምር ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሲቪል የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ቻይናዊያን ለዓለም በኮሮና ቫይረስ ትግል አስተምረዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞች በፍልሚያው ውስጥ ቀጥታ በመግባት ቻይናን እና ዓለምን ከቫይረሱ የመከላከል ሥራ መሥራታቸው የሚወደስ ነው።
የተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በጥቂት የሰው ኃይል በመስራት፣ ከቤት ሆነው ሠራተኞች የዕለት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ፣ በየተራ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የመከላከል ሥራውን በከፍተኛ ሁኔታ ማገዛቸው ከቻይና ቢወሰደ የሚጠቅሙ ምክሮች እንደሆኑ ማየት ይቻላል።
ከዚህም በመነሳት ኢትዮጵያ ጠንካራ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት የህግ አስፈፃሚ አካላትን አቅም ማጎልበትና ማደራጀት ይገባል።
የቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ግንዛቤ መፍጠር፣ የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ማደራጀትና አስፈላጊውን የህክምና መርጃ ቁሳቁስ ከወዲሁ በፍጥነት ማሟላት አስፈላጊ እንደሆነ አመላክተዋል።
ወቅታዊና አስፈላጊ የሆኑ ስትራቴጂዎችን፣ ዘዴዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል፤ የተማከለ፣ ነፃና ግልፅ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ፤ ቫይረሱ ሲከሰትም ሳይረበሹ አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት መስጠትና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ህብረተሰቡ የግልንና የአካባቢውን ንፅህና በየዕለቱ መጠበቅ እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎችና መንግስት የሚሰጡትን መመሪያ በትኩረት መከታተልና መተግበር ይኖርበታል።
በተለይም የመከላከል እርምጃዎችን ሳይዘናጉ መተግበር፣ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ በየጊዜው የግል ንፅህና መጠበቅ የሚቻለው እቤት መሆን፣ ከሁሉም በላይ እርስ በርስ መደጋገፍና መተባበር ያስፈልጋል፡፡
''የህብረተባችን መዘናጋት አሳሳቢና ለቫይረሱ መሰራጨት በር የሚከፍት ነው። ስለሆነም ህብረተሰቡ ለወረርሺኙ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል'' ብለዋል፡፡
በመንግስትና በሚዲያ በኩል ሳያሰልሱ የመከላከያ መንገዶችን ማሳወቅ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር፣ አስፈላጊ ሲሆን አስገዳጅና ህግ የሚተላለፉትን በህግ እስከመጠየቅ የሚደርሱ እርምጃዎችን መውሰድ የግድ እንደሚልም ተናግረዋል።