በድሬዳዋና አዳማ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋና አዳማ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ
ድሬዳዋ/ አዳማ / ሚያዝያ 25/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋና አዳማ ከተሞች ለ700 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ተደረገ።
በድሬዳዋ የሣቢያን ቀበሌ ወጣቶች ባሰባሰቡት ከ370 ሺህ ብር በላይ የገዙትን የምግብ ቁስቁስ ለ500 አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ድጋፍ ማድረጋቸውን የወጣቶቹ አስተባባሪ ነፃነት ጥላሁን ለኢዜአ ገልጿል።
ድጋፉ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ዕለታዊ፤ የምግብ ፍጆታቸውን ማግኘት ላልቻሉ ቤተሰቦች የተሰጠ ነው ብሏል፡፡
የአካባቢው ወጣቶች ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በድምጽ- ማጉያ መሳሪያ በመታገዝ ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ በማስተማር ላይ መሆናቸውንም አመልክቷል።
ወጣቶቹ ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት የአካባቢው ቀበሌ ዋና ሥራ አስፈፃሚና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ወንድማገኝ በሻህ ወጣቶቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ድጋፉ ከተሰጣቸው መካከል ወይዘሮ ነጂባ መሐመድ በሰጡት አስተያየት ወጣቶቹ ያደረጉላቸውን ድጋፍ ደጋፊ ለሌላቸው ህፃናት ልጆቻቸው ምግብ ለመሸፈን እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
"የሰጡንን እጆች አላህ ይባርካቸዋል፤ የረመዳን ፆም የመልካምነትና የመደጋገፍ ወር በመሆኑ የወጣቶቹ ዋጋ ከፍ ያለ ነው" ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በመከላከያ ሚኒስቴር የምስራቅ ዕዝ ኢንዶክትሬኔሽን ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዳይሮክቶሬት አባላትና አመራሮች ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ አደባባዮችና ጎዳናዎች በመዘዋወር ህብረተሰቡ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ አከናውነዋል፡፡
የዳይሬክቶሬቱ ኃላፊ ተወካይ ሻምበል ዳንኤል አወል ሠራዊቱ ራሱንና ቤተሰቡን ከመጠበቅ ባሻገር ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ እራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ ማስተማራቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ አባላት ከ300ሺህ ብር በላይ የሚገመት የተለያየ ቁሳቁስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ አደርገዋል።
የፖሊስ አባላቱ ያደረጉት ድጋፍ ቁጥራቸው 200 ለሆኑ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ነው።
የአዳማ ከተማ ከንቲባና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አሰግድ ጌታቸው እንደገለጹት የፖሊስ አባላት ህግ ከማስከበር በተጓዳኝ በቫይረሱ ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች እንዳይጎዱ መደገፋቸው ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ያረጋገጠ ተግባር ነው።
በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈፀም ረገድ አሁንም አባላቱ በሙሉ አቅማቸው መረባረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በከተማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማስፈፀም ጎን ለጎን መንቀሳቀስ ለማይችሉ አቅመ ደካሞች በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ቶሎሳ ኃይሉ ናቸው።
ካደረጉት ድጋፍ መካከል የምግብ ዘይት፣ሩዝ፣ማካሮኒና አልባሳት ይገኙበታል።
ህብረተሰቡ እራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ በከተማው የተለያዩ አገልግሎት መስጪያ አካባቢዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየሰሩ መሆናቸውንም ኮማንደር ቶሎሳ ገልጸዋል።