ኢንዱስትሪ ፓርኩ ኮሮናን በመከላከል ስራዎቹን በማቀላጠፍ ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪ ፓርኩ ኮሮናን በመከላከል ስራዎቹን በማቀላጠፍ ላይ ነው
ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 24/ 2012 (ኢዜአ) የይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል አጠቃላይ ስራዎቹን በጥንቃቄ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ ፡፡
የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን ለኢዜአ እንደገፁት አራት ሼዶችን ጨምሮ የአስተዳደርና የሥልጠና ማዕከል ህንፃዎች ስራ ያካተተው የፓርኩ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ ተጠናቅቋል ።
የመሠረተ ልማት ሥራዎች የሚከናወኑበት ሁለተኛው ምዕራፍ ከ70 በመቶ በላይ መከናወኑንና የሶስተኛ ምዕራፍ ሥራዎች አካል የሆነው የሰባት ሼዶች ግንባታ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ነው ምከትል ዋና ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት።
እስከ አሁን ድረስ 11 የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ውል በመግባት የተጠናቀቁ ሼዶችን ወስደው የመሳሪያዎች ተከላ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል ።
ከእነዚህ መካከል በአካባቢው የሚመረተውን አቮካዶ ከአርሶ አደሮች በመረከብ ዘይት የሚያመርተው “ ሳልቫዶ ማኒፋከቸሪንግ ” ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ማምረት መጀመሩን አስረድተዋል።
ኩባንያው በስድስት ዙር ከ150 ቶን በላይ የአቮካዶ ዘይት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ 800 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱን ገልጸዋል።
በኩባንያዎችም ሆነ በፓርኩ ግንባታ ሥራ ላይ በርካታ ባለሙያዎችና የጉልበት ሰራተኞች እንደተሰማሩ የገለፁት አቶ ናትናኤል የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በኮርፖሬሽኑ የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው በቀለ የፓርኩ ማስተር ፕላን አካል የሆነው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ከግንባታ ሥራዎች ያልተናነሰ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በአረንጓዴ ልማትና ውበት ሥራ 67 ማህበራት የሚሳተፉ ሲሆን ባጠቃላይ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎችና የጉልበት ሰራተኛች ይሰማራሉ።
በዘንድሮ የተከላ ወቅት ከ24 ሺህ በላይ ችግኞችን በፓርኩ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
አሁን ላይ በርካታ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ዳይሬክተሩ ሰራተኞች ከወትሮው በተለየ መልኩ በቂ ርቀት ኖሯቸው ተነጣጥለው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በርካታ የሰው ኃይል ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጋችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሌሎች ዘርፎች ላይ ባስከተለው መቀዛቀዝ አካባቢው ላይ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል ነው ያሉት።
የሳልቫዶ ማኒፋከቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ፕሮዳክሽን ማኔጀር ሚስተር ኦኬ ማይ ደግሞ ወቅቱ የአቡካዶ ምርት የሚሰበሰብበት ባለመሆኑ ፋብሪካው ሥራ ማቆሙንና የጥገና ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በዚህም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚጠቅሙ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በማድረግ የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ነው ያስረዱት።
አሁን ያለው የዝናብ ወቅት እንዳለፈ ወደ ምርት ሥራቸው ዳግም ተመልሰው እንደሚገቡ የገለፁት ሚስተር ኦኬ ሥራ ሲጀምሩ በፋብሪካው ውስጥ ሰዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጠብቀው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ይደረጋል ብለዋል።
በፓርኩ ውስጥ እየሰሩ ከሚገኙ መካከል ወጣት ለገሰ ሽፈራው በሰጠው አስተያየት ከዚህ በፊት በአካባቢው በርካታ ሰዎች ሥራ አጦች እንደነበሩ ገልፆ በፓርኩ አማካይነት በተፈጠረላችው ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል።
የችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየቆፈሩ እንደሚገኙ የገለፀው ወጣት ለገሰ በስራቸው ወቅት ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ በማድረግ ተራርቀው እያከናወኑ መሆናቸውን ነው ያመለከተው።