ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አዋጁን በመጣስ የጋብቻ በዓሉን ሲከብር የነበረ ግለሰብ ተቀጣ

ድሬዳዋ ሚያዚያ 25 2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላን  በመጣስ  ሶስተኛ ዓመት  የጋብቻ በዓሉን ሲያከብር የነበረ  ግለሰብ መቀጣቱን  የአስተዳደሩ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።

በድሬዳዋ ቀበሌ አምስት  የሚኖረው ግለሰቡ  ከባለቤቱና 12 ወዳጆቹ ጋር በመሆን ሶስተኛ ዓመት የጋብቻ በዓሉን እያከበረ ነበር ፡፡

ሆኖም የግለሰቡ ድርጊት ለኮሮና ቫይረስ የሚያጋልጥ ተግባር መሆኑን በሚመለከተው የፀጥታ ግብረ ኃይል ተነግሮታል፡፡

በተጨማሪም ድርጊቱ ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ደንብ የሚጥስ መሆኑን እንደተገለጸለት የግብረ ኃይሉ አባልና የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ስራዎች ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ  ለኢዜአ ገልጸዋል።

"ሆኖም ችላ በማለት በድርጊቱ እስከ ሌሊት ሊቀጥል ችሏል፤ ግብረ ኃይሉም  ግለሰቡን በቁጥጥር ስር በማዋል ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ የሆነውን ትዕይንት በትኗል" ብለዋል፡፡

እንደ ኮማንደር ገመቹ ገለጻ ግለሰቡ በአዋጁ የተከለከለውን ድርጊት መፈጸም የቀረበበትን ክስ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 3 ሺህ ብር ቀጥቶታል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም አዋጁን በመተላለፍ አቃቤ ህግ  ክስ በመሰረተባቸው አራት ግለሰቦች እና ሁለት ተቋማት  እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ አምስት መቶ ብር እስከ 32 ሺ ብር ቅጣት አስተላልፏል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ሬስቶራንት ሲሆኑ በቂ ርቀት ሳያስጠብቁ  ያልተፈቀደ አገልግሎት ሲሰጡ ተደርሶባቸው እያንዳንዳቸው ከ15 ሺህ እስከ 32 ሺህ ብር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ናቸው።

ከዚህም ሌላ ለቫይረሱ በሚያጋልጥ ሁኔታ ጫት በማስቃምና ሺሻ በማስጤስ ተግባራት ተሰማርተው የነበሩ ሶስት  ግለሰቦች  እያንዳንዳቸውን በ2ሺህ አምስት መቶ ብር እንደተቀጡም ኮምንደሩ አመልክተዋል።

ግብረ ኃይሉ  የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች ለማስከበር የተቀናጀ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም