ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ መመሪያ አለመተግበሩን ወላጆች ገለጹ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2012 (ኢዜአ) መንግሥት በግል ትምህርት ቤቶች ተፈፃሚ እንዲሆን ያወጣው የአከፋፈል መመሪያ አለመተግበሩን ወላጆች እየገለጹ ነው።
መንግሥት በዓለም ብሎም በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ በማድረግ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ተማሪዎችም ቤታቸው እንዲቀመጡ ተደርጓል።

ታዲያ በዚህ ወቅት የግል ትምህርት ቤቶችና ወላጆችን ያወዛገበው የትምህርት ክፍያ ዋነኛው ጉዳይ ሆኗል።

ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሳይሔዱና በትምህርት ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ወርሃዊ ክፍያ መጠየቃቸው አግባብ እንዳልሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የአዲስ አበባ ከተማ ወላጆች ይናገራሉ።

ትምህርት ቤቶች ደግሞ የመምህራን ደሞዝና የቤት ኪራይ ወጪዎች መሸፈን ስላለብን ወላጆች ''ተገቢውን'' ክፍያ መፈፀም አለባቸው ይላሉ።

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን መነሻ በማድረግም ሚያዝያ 12 ቀን 2012 ባወጣው መመሪያ ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ከ50 እስከ 75 በመቶ የሚሆነውን ክፍያ እንዲፈጽሙ ወስኗል።

ቀደም ብሎ በርካታ ትምህርት ቤቶች ወላጆች ሙሉ ክፍያ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።

ሚኒስቴሩ መመሪያውን ካስተላለፈ ወዲህ ወላጆች ለክፍያ የተቀመጠውን የመጨረሻ ጣሪያ በመጠቀም 75 በመቶና ከዚያ በላይ በማስከፈል ላይ ናቸው።

አንዳነድ ትምህርት ቤቶች የልጆቻቸውን ክፍያ ካላጠናቀቁ በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ የትምህርት ማስረጃ አንሰጥም እያሉ በማስፈራራት ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል።

ወላጆቹ እንደሚሉት መንግሥት ክፍያ ለመፈጸም አቅም የሚያንሳቸው ወላጆች ክፍያውን እንደሚሰረዝ ቢገልጽም፤ይህንን የሚተገብር ትምህርት ቤት የለምም ይላሉ።

ከዚህ ባለፈ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ መንገዶችን ትምህርት ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት ወጥነት ስለሚጎድለው መፍትሄ እንዲቀመጥለት አሳስበዋል።

በተለይም የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነት ዝቅተኛ በሆነበት አግባብና በማህበራዊ ሚዲያ

(በቴሌግራም) የሚላከውን ትምህርት በርካታ ወላጆች ለመጠቀም ስለማይችሉ የትምህርት አሰጣጡን መና አስቀርቶታል ብለዋል።

መንግሥትም የተማሪዎቹን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሰመረ ለማድረግ አማራጮች እንዲፈለግ ወላጆቹ ጠይቀዋል።

ትምህርት ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ባለው ድርሻ ችግሮቹ ፈጣን ምላሽ ስለሚያስፈልጋቸው የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም