ቀጥታ፡

የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ 111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ዘርፉን ተቀላቅለዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24/2012(ኢዜአ)የኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ከተከሰተ በኋላ ለ111 የንጽህና መጠበቂያ አምራቾች ፍቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣን አስታወቀ። 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ በህብረተሰቡ ዘንድ የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች ፍላጎት ጨምሯል።

በወቅቱ የፍላጎቱና የምርት መጠን ባለመመጣጠኑ በተለይም የሳኒታይዘርና የአልኮል ምርት እጥረት አጋጥሞ ነበር።

ችግሩን ለመፍታት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ ከተሰማሩና ፍላጎት ካላቸው አምራቾች ጋር ውይይት ማካሄዱንም አስታውሰዋል።

በዚህም አምራቾች ሳኒታይዘር እና አልኮል በስፋትና በጥራት እንዲያመርቱ የሚያስችል ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ የገቡበት ሁኔታ መኖሩን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት።

ባለስልጣኑም አምራቾቹ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ ሳኒታይዘር እና አልኮል በስፋት እንዲያመርቱ ለማስቻል የሚያግዝ ጊዜያዊ መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ አድርጓል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት መመሪያው አምራቹ ስለምርቱ ሁኔታና ጠቀሜታ የሚያቀርበው ፕሮፖዛል በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችልና የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱም ፈጣን እንዲሆን የሚያግዝ አሰራርን በውስጡ አካቶ የያዘ ነው።

በዚህ መሰረት ዘርፉን በመቀላቀል የጥራትና የግብአት መስፈርቱን ላሟሉ 111 አምራች ፋብሪካዎች ወደምርት እንዲገቡ ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል።

"ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ወቅት የሳኒታይዘርና የአልኮል ምርቶቻቸውን በጥራትና በሚፈለገው መጠን በማምረት ለህብረተሰቡ እያቀረቡ ይገኛሉም" ብለዋል ዳይሬክተሯ።

የምርቶቹን የጥራትና የደረጃ ሁኔታ ለመከታተልም በጊዜያዊነት የተዘጋጀው መመሪያ የቅኝት ስራን የሚያከናውኑ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ዝርዝር ሁኔታ ጭምር የሚዳስስ ነው።

የቅኝት ስራውን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሙያተኞች በተጨማሪ ከአዲስ አበባ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለስልጣን እና ከጸጥታ አካላት የተወጣጣ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የሚሰሩበት ሁኔታም ተፈጥሯል።

ወይዘሮ ሄራን እንዳሉት የቅኝት ሥራው በገበያ ስፍራዎች፣ በሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቆች፣ በሱፐር ማርኬቶችና በመድኃኒት ቤቶች የሚከናወን ነው።

በተከናወነው የቅኝት ስራም አጠራጣሪና ከደረጃ በታች የሆኑ፣ እውቅናና የንግድ ፈቃድ የሌላቸው እንዲሁም የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምርቶችን በፍተሻ መያዝ ተችሏል።

"በዚህም ባለስልጣኑ እነዚህን ምርቶች ከገበያ የመሰብሰብና የማስወገድ ሥራ እና አቅራቢዎቹንም ተጠያቂ የማድረግ ተግባር አከናውኗል" ይላሉ።

በቁጥጥር ሥራው እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የተወሰኑ አምራቾች የምርት ጥራታቸውን በማሻሻል በአዲስ መልክ ወደ ምርት ለመግባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም