የነገ እንጀራችን… በምጣዳችን - ኢዜአ አማርኛ
የነገ እንጀራችን… በምጣዳችን
በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)
ሁለት ዓይን ለዓይን የሚተያዩ የተራራ ሰንሰለቶችን ያገናኘና 145 ሜትር ከፍታ እንዲሁም 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ደብረ ማርቆስ፣ እንጅባራና ቻግኒ ከተሞችን በማቋረጥ በ730 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወይም ደግሞ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ ነቀምትና አሶሳ ከተሞችን በማቋረጥ በ830 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአባይ ወንዝ ውሃ የመጠቀም የኢትዮጵያውያን መብት ላይ ተገንብቶን የኖረውን ግንብ የደረመሰ፣ በአባይ ወንዝ ውሃ መጠቀም አለመቻል የፈጠረውን የረጅም ግዜ ቁጭት የሻረ የአሸናፊነት ምልክት ነው። ግድቡ የጥንት ኢትዮጵያውያን ደርሰውበት የነበረውን የስልጣኔ ደረጃ፣ የቅድመ አያቶቻችን በአድዋ ተራራ መሃል የፈፀሙትን አንፀባራቂ ድል የአሁኑ ትውልድ በጉባ ተራሮች መካከል እየደገመ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የአንድነት፣ የእድገት ተነሳሽነታቸውና መፃኢ ህዳሴያቸው የሚገልፁበት፣ የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫ ታሪካዊ ሃውልትም ነው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሕዳሴ ግድባችን ከዕለት ጉርሳችን ቀንሰን በተባበረ ክንድ እየገነባን እዚህ ያደረስነው ብቻ ሳይሆን የማድረግ አቅማችንን ያሳየንበት ትልቁ ጸጋችን ነው ሲሉ የገለጹት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የግድቡን ዘጠነኛ አመት አስመልከቶ ባስተላለፉት መልዕክት ለግድባችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጠው አንድም የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ ሁለትም የትሥሥራችን ገመድ በመሆኑ ጭምር ነው" ብለዋል፡፡
ይህ እኛ ኢትዮጵያዊያን እየገነባን ያለነው ግድብ እናቶች ምጣድ አስሰው ሊጥ ቀብተው አስፈላጊውን እክብካቤ እያደረጉለትና እሳት እየቆሰቆሱበት እስኪበስል በስስት እንደሚጠባበቁት እንጀራ፤ ልጆች እንጎቻ በስሎ እስኪበሉ እንደሚጠባበቁት ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ግድቡን በምጣድ ላይ እንዳለ እንጀራ በስስት የምናየው ሀሴት ነው።
ግድቡ ለምግብነት ለመድረስ አሁንም የሚቀር ከፍተኛ ሥራ ቢኖርም የሚቀረው ጊዜና ሒደት እንዳለፈው የሚከብድ ባለመሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ በሚችለው መጠን ሁሉ ግንባታውን ለማጠናቀቅ መረባረብ የግዴታ ውዴታ አለበት።ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሰብሳቢና የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ግድቡ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ፍሬ ለመቅመስ የተጓዝነው ብዙ፤ የቀረው ትንሽ ነው" ሲሉ የተናገሩት።ዶክተር አብርሃም አክለውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የብሔራዊ ቁጭታችን እልባት የሚያገኝበት የመጨረሻ ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ወንዞቿ ያላትን ውሃ ለረጂም ዘመናት በአግባቡ ያለማልማትና ሳትጠቀም መቆየቷ፤ በታችኞቹ የተፋሰስ ሃገራት የክልከላ ምክንያት ብቻም ሳይሆን አገሪቷ ውሃውን መጠቀም የሚያስችላት በቂ የካፒታል አቅም ከራስዋ ማመንጨት የማትችል ደሃ ሃገር በመሆኗም ጭምር ነበር። ኢትዮጵያውያን አሁን የህዳሴውን ግድብ መገንባት የጀመሩት ሱዳንና ግብፅ ኢትዮጵያን ሳያካትቱ የገቡት 1929 እና የ1959 ዓ.ም የውሃ ድርሻ ስምምነት ስለተቀየረና ለኢትዮጵያ በውሃው የመጠቀም እውቅና ስለሰጡም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ግድቡን በራሳችን ሃብት ለመስራት በመወሰናችን እንጂ።
ስለሆነም ነው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከመጋቢት 24/2003 ዓ.ም አንስቶ በከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ በመገንባት ላይ የሚገኘው። ግድቡ ከሚያስገኘው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በላይ መላው ኢትዮጵያንን ያለምንም ልዩነት በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰቡ በሀገራችን የብሔራዊ መግባባት መፍጠሪያና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከሪያ ከመሆኑም በላይ የይቻላል መንፈስ ተላብሰን ታላላቅ ልማቶችን እንድንደፍር በማድረጉ የሀገራችንን በጎ ገጽታ በመገንባት ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል።
የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በገጠር በሚገኘው ማህበረሠብ ዘንድ
ትልቅ የአኗኗር ለውጥ ይፈጠራል። ምግብ ለማብሠል ከአመድ እና ጭስ ጋር ሲታገሉ
የሚውሉ እናቶች በቀላሉ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ምድጃ በማብሰል ወደዘመናዊ የአኗኗር ዘዴ መለወጥ ያስችላል። በእርግጥ የመብራት መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን ከነጭራሹም መብራት የሌላቸው አካባቢዎች መኖራቸው በምጣኔ ኃብቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። ፋብሪካ ከፍቶ መብራት “ይመጣ ይሆን ይቀር?” እያለ ቀኑን ሙሉ ስጋት ውስጥ ወድቆ የሚውል ባለሀብትም ሞልቷል።
በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚያመለክተው በዘንድሮ ክረምት የመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌት እንደሚከናወንና በዚህም 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚያዝ ይገልጻል።
የመጀመርያው ዙር ሙሌት ሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በቀጣዩ ክረምት ማለትም በ2013 ዓ.ም. የዝናብ ወቅት ለሁለት ወይም ሦስት ወራት እንደሚከናወንና 13.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃም በዚህ ወቅት እንዲሞላ ተደርጎ፣ የመጀመርያው ዙር ሙሌት እንደሚጠናቀቅ ሰነዱ ያስረዳል።
በዚህ ዙር የሚደረገው የውኃ ሙሌት በአጠቃለይ 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በግድቡ እንዲጠራቀም በሰነዱ የተገለጸ ሲሆን የመጀመርያዎቹ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ፣ እንዲሁም ሌሎቹ ተርባይኖች ላይ የኃይል ማመንጨት ሙከራ ለማድረግ እንደሚያስችል ታውቋል።
ኢትዮጵያ ይኼንን የውኃ አሞላል ሒደት የቀረፀችው የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳያደርስ በመጠንቀቅ መሆኑን የሚያመለክተው ሰነዱ፤ ኢትዮጵያ ራስ ወዳድና ለሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ግድ የሌላት ቢሆን ኖሮ፣ 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነውን የውኃ መጠን በሦስት ዓመታት ውስጥ መሙላት የምትችል መሆኑን ይገልጻል።
በግብፅ መንግሥት በኩል የተያዘው አቋምና በግብፅ ሚዲያዎች የተያዘው ዘመቻ የኢትዮጵያን በውሃዋ የመጠቀም መብት የሚክድ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ ባልሆነችበት የቅኝ ግዛት ውል ለመጫን ያለመ እንደሆነም ሰነዱ ያትታል። ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷ በምንም ዓይነት ምክንያት የማይጣስ እንደሆነ የሚገልጸው ሰነዱ፣ የህዳሴ ግድቡና በዓባይ ውኃ መጠቀም ለኢትዮጵያ የሞትና ሽረት ጉዳይ መሆኑንም አመልክቷል።
የግድቡን የውኃ አሞላል ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በማምታታት ጉዳዩን ፖለቲካዊ በማድረግና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን በማግኘት ኢትዮጵያን መጠምዘዝ፣ መቼም ቢሆን ሊሳካ የማይችል ጥረት እንደሆነ ያመላከተው ሰነዱ፤ግድቡ እውን ሆኖ ስራ ሲጀምር ለቀጠናው ሀገራት ተጨማሪ የኃይል ምንጭ ከመሆኑም በላይ የተሻለ የውሃ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያደርግ አትቷል።
በሰነዱ ላይ እንደተገለጸው ይህ ግድብ እውን ሲሆን ለታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ከሚሰጣቸው በርካታ ጥቅሞች መካከል የውሃ ትነትን በመቀነስ የተመጠነ ውሃ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የውሃ ጨዋማነትን በመቀነስ ለአሳ ሀብት ልማት እንዲውል ያደርጋል፣ ጎርፍን በመቀነስም ምቹ የሰዎች ኑሮን ያደላድላል።
በተጨማሪም ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃው በተመጠነ መልኩ እንዲፈስ በማድረግ ለመስኖ ልማት ያግዛል፣ ለሱዳን ግድቦች የተመጠነ ውሃን በመልቀቅ አቅማቸውን ያጎለብታል፣ ለቱሪዝም ፍሰት ጉልህ ሚና ይቻወታል። የታችኞቹን አገራት የግድቦችን አቅም በማጎልበት አላስፈላጊ ወጭንና ጭንቀትን ይቀንሳል፣ አላስፈላጊ የውሃ ስርገትን ከመከላከል በተጨማሪም በየዓመቱ በሱዳን የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግድቦች የሚከማቸው ደለል እንዲቀንስ ያግዛል ሲልም ሰነዱ ያብራራል።
ግድቡ ለአገራችን በዋናነት ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ለአሳ ሀብት ልማትና አካባቢያዊ ውሃ ፍጆታ እንዲኖር ከማገዙም በላይ በአጠቃላይ የግድቡ እውን መሆን ለኢትዮጵያ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች በብዙ እጥፍ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት በተለይ ለሱዳን እና ለግብጽ ጥቅሙ የጎላ እንደሆነም በሰነዱ ሰፍሯል።
የውኃ ኃይል ማመንጫ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ነፃ በመሆኑ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢ ሥነ ምኅዳርንም በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም በባለሙያዎች ተገምግሟል። ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከመጀመሯ በፊት ለሱዳን እና ለግብፅ ግድቡን በጋራ የመገንባት ሀሳብ አቅርባ እንደነበር የግድቡን 9ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ተንታኞች እና በአረብኛ ቋንቋ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። ተሳታፊዎች በዚሁ ወቅት ሱዳን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘችው አቋም የጋራ ሀብትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ጠቅሰው። ሱዳን ይህን ያደረገችው በግድቡ ግንባታ ከጉዳቷ ይልቅ ጥቅሟ እንደሚጎላ በማረጋገጧ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ግብፅ አሁንም ድረስ የያዘችው ያፈነገጠ አቋም ኢትዮጵያን ሳታሳትፍ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈራረመችውን ኢ-ፍትሃዊ ውል በኢትዮጵያ ላይ በግድ ለመጫን ያላትን የቆየ ምኞት ያሳያል ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ ለአረቡ ዓለም በተለይም ለግብጻውያን ግልፅነት ለመፍጠር በአረብኛ ለሚሰሩ ጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙኃን መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ግብጽ ያላት አገራዊ የኢሌክትሪክ ሽፋን ከ45ሺህ ሜጋ ዋት በላይ እንደሆነ ያስረዳው ሰነዱ፤ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ አገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋን ጋር ሲነጻጸር በአስር ዕጥፍ ብልጫ እንዳለው ያሳያል። ይህም በመሆኑ አሁን እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ እንዳይጠናቀቅ መጣር የአገሪቷን የቆየው እኔ ብቻ ልጠቀም አይነት ዝንባሌ የያዘ ዘመኑን ያልዋጀ አስተሳሰብ እንደሆነም በሰነዱ ላይ ተገልጿል። ለዚህም በርካታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ግብጽ በናይል ወንዝ ያላትን ሃላፊነት የጎደለው ተጠቃሚነትን ያጎላ ፍላጎት እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል።
በመሆኑም ግደቡ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት አሁን በኢትዮጵያ ያለውን አቅም ውደ 11 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል እንደሚያሳድገውና አጠቃላይ የሀገሪቷን የሃይል ስርጭት ከ41 በመቶ ወደ 75 በመቶ እንደሚያሳድገው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
“ፍቅር ካለ” እንዲሉ የተጀመረውን የህዳሴ ግድብ ዳር ማድረስ የአገሪቷን ብሎም የጎረቤት አገራትን የጋራ ተጠቃሚነትን ስለሚያረጋግጥ፤ ከመፎካከር ይልቅ መተጋገዝ የውዴታ ግዴታ በመሆኑ የተፋሰሱ አገራት ትብብርና የአብሮነት ስሜት ሊዳብር ግድ እንደሚል የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ የአባይ ወንዝ በከንቱ መፍሰስና በበይ ተመልካችነታችን ሲቆጭ የኖረው እና ቁጭቱን በእንጉርጉሮ፣ በስነቃሎች እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፉን በገንዘብ፣ በሙያው፣ በጉልበቱ ለማረጋገጥ በገባው ቃል መሰረትም በቦንድ ግዥ፣ በስጦታ፣ እንዲሁም በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡
ግንባታው በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ ታጅቦ ወሳኝ ምዕራፎችን እየተሸጋረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ጥቅል ግንባታው ከ73 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቀ የህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ አክለውም ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ሥጋት በዓለም ላይ ጥላውን ያጠላ ቢሆንም የህዳሴው ግድብ ሥራ በነበረው ግለት እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥቅሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህዝብና የመንግሥት ጥብቅ ትስስር የተገለጸበት ውጤታማ ፕሮጀክት ነው እና በእርግጥም ታላቅ ነው። የሀገር እና ህዝብ ራእይ እውን የሚሆንበት ብቻ ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳውም የጎላ ነው። የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ድልን መቀዳጀት ብቻ ሳይሆን፤ ከድህነት ለመውጣት ለምትታር ሀገር ይቅርና ለአደጉትም ሀገራት ቢሆን ብርቅዬ ነውና አሁንም ድጋፋችንን ልንቸረው ይገባል። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደ ምጣድ እንጀራ ብቻም ሳይሆን እንደ ዓይናችን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል መልዕክታችን ነው።