ቀጥታ፡

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋወሩ የነበሩ 33 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ፍቼ ፣ሚያዚያ 24/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋወሩ የነበሩ 33 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው አዛዥና የኮረና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል ኮማንደር ታሪኩ ድርበባ ዛሬ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ ጥሰው ወንጀል በመስራታቸው ነው።

በዚህም 18 ክላሽንኮቭ፣ 19 ኤስ ኬ ኤስ ጠመንጃዎችንና 24 የተለያዩ ሽጉጦች ከግለሰቦቹ ላይ መገኘቱን አስታውቀዋል።

እንዲሁም  6 ቦንቦችና 1 ሺህ 495 የተለያዩ ጥይቶችን በህገ ወጥ መንገድ ለስውር ዓላማ በመኖሪያ ቤታቸውና በስራ ቦታቸው ደብቀው እንደተገኙም አመልክተዋል።

"ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ከህብረተሰቡ በደረሰን ጥቆማ በተደረገው አሰሳ ከተያዙት 33 ግለሰቦች መካከልም በተለያዩ የአስተዳደር እርከን ላይ ያሉ አመራሮች ተሳታፊ ነበሩ" ብለዋል።

ከነዚህ ውስጥ የአንድ ቀበሌ ሊቀ መንበር ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመሸጥና በማዘዋወር ቀጥታ ተሳታፊ ሆኖ መገኘቱን አዛዡ አስረድተዋል።

የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ በተለይም በደራና ወረ ጃርሶ ወረዳዎች   እየተበራከተ በመምጣቱ ለነፍስ ግድያ፣ ለዘረፋና ለሌሎች የወንጀል  ተግባራት ዳርጎናል  ህብረተሰቡንም ለጸጥታ ስጋት አጋልጦ እንደነበርም  አዛዡ  አስታውሰዋል።

መንግስትና ህዝቡ ኮሮናን ለመከላከል በርብርብ ላይ ባሉበት በዚሀ ወቅት ግለሰቦቹ በዚህ መሰል ህገወጥ ተግባር ላይ መሳተፋቸው እንዳሳዘናቸውና መንግስት ቁጥጥሩን ማጠናከር እንዳለበት  ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም