ቀጥታ፡

በኤሌክትሪክ መቋራረጥ መቸገራቸውን የሰሜን ሸዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ነዋሪዎች ገለጹ

ፊቼ፣ ሚያዝያ 24/2012 (ኢዜአ) የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት በተደጋጋሚ መቋራረጥ ችግር እንደፈጠረባቸው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ነዋሪዎች ገለጹ።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል  የደብረ ፅጌ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ በላይ ፈጠነ እንዳሉት የላቦራቶሪ ማሽኖችና የህክምና መሳሪያዎች ማፅጃ ማሽኖች በኃይል መጥፋት ምክንያት ታካሚዎችና ተገልጋዮች እየተቸገሩ ነው።

በተለይም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል አኳያ ለባለሙያዎችና ለተገልጋዮች የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ሌላው ነዋሪ የፍቼ  ንግድ ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አብረሃም በበኩላቸው ኮምፒዩተሮች፣ የማባዣ ፎቶ ኮፒና የሒሳብ ማሽኖች በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ስለማይሰሩ ባለጉዳዮች እየተጉላሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ኮሮናን ለመከላከል በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ወቅታዊ መረጃዎችን ህብረተሰቡ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ምክንያት ለመከታተል እንዳልቻለ የተናገሩት ደግሞ በፍቼ ከተማ የቀበሌ አራት ሊቀ መንበር አቶ ቸርነት ጥላዬ ናቸው።

በደብረ ሊባኖስ እና ሙከ ጡሪ ከተሞች  የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ከመቆራረጥ አልፎ ስለሚጠፋም  የውሃ፣  የህክምና እና የእህል ወፍጮ አገልግሎት በማጣት መቸገራቸውን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፍቼ ዲስትሪክት ሰብ ስቴሽን ኃላፊ ወይዘሪት ዘውዴ ተፈራ በሰጡት ምላሽ ችግሩ ከሚያዚያ መጀመሪያ አንስቶ ከገፈርሳ ኃይል ማመንጫ በሚመጣው መስመር ላይ ብልሽት በመከሰቱ የተፈጠረ   መሆኑን ገልጸዋል።

"ከዋናው መስሪያ ቤትና ከዲስትሪክቱ ባለሙያዎች ተልከው መፍትሔ ለመስጠት እየተረባረቡ ናቸው" ብለዋል።

በአካባቢው ንፋስ፣ ዝናብና አንዳንዴ ህገወጥ ግለሰቦች በኃይል ተሸካሚ መስመርና ማስተላለፊያዎች ላይ ጉዳት እንደሚደርስ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ በአፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የባለሙያ እና ቴክኖሎጂ እጥረት በመኖሩ ችግሩ በተደጋጋሚ እንዲፈጠር እንዳደረገውም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም የህዝብና የመንግስት ንብረት የሆነውን የኃይል ማስተላለፊያ መሳሪያዎችን ከጉዳት መጠበቅ እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም