ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን የግብርና ስራው ቀጥሏል

ደሴ ፣ ሚያዚያ 24/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን የከሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎን ለጎን ለመስኖ ልማትና ለመኽር እርሻ ዝግጅት የተጠናከረ ድጋፍ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በለጋምቦ ወረዳ በ161 ሄክታር መሬት ላይ በዘመናዊ መስኖ የለማው የስንዴ ሰብል ተጎብኝቷል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በዚህ የበጋ ወቅት 130 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለምቷል።

ከለማው መሬትም እስከ አሁን ድረስ ከ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥም ለግማሽ ሚሊዮን ኩንታሉ የገበያ ትስስር በመፍጠር እጥረቱን በተወሰነ መልኩ መፍታት መቻሉን ገልፀዋል።

የዚህ ጉብኝት ዓላማም የስንዴ ሰብሉ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትና ለምግብ እህል አቅርቦት ተሞክሮ የሚቀመርበት ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም ተናግረዋል።

የለጋምቦ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመድ ጋሻው እንደገለጹት በዚህ የበጋ ወቅት አንድ ሺህ 400 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ለምቷል።

ዛሬ የተጎበኘው 161 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መስኖ የለማ ስንዴ ሰብል 500 የሚጠጉ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን ከአራት ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ እንዳሉት ከኮሮና መከላከል ጎን ለጎን ኢኮኖሚውን በግብርናው ዘርፍ ለማነቃቃት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

አርሶ አደሩ በመስኖና በበልግ በዘራው ሰብል ውጤታማ እንዲሆንና ራሱን ከኮረና ቫይረስ እንዲጠብቅ የኢኮኖሚ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ቤት ለቤት በባለሙያ እንዲደገፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በኮሮና መከሰት ሊፈጠር በሚችል የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ህብረተሰቡ ለርሃብ እንዳይጋለጥም ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አቅም በፈቀደ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

የመስኖና የበልግ ሰብል ልማት ስራውን አርሶ አደሩ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከማድረግ ባለፈም ለመኽር እርሻ የሚውል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ እንዲቀርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት ሙያዊ ድጋፍ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው አርሶ አደሩም እራሱን ከበሽታው በመጠበቅ የእርሻ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በመስኖ ሰንዴና የቢራ ገብስ እያለሙ መጠቀም ከጀመሩ ሁለት ዓመታት እንደሆናቸው የገለፁት ደግሞ በወረዳው የቀበሌ 20 ነዋሪ አርሶ አደር ስዩም አዛዥ ናቸው።

ከዚህ በፊት በባህላዊ መንገድ ማልማታቸው በልፋታቸው ልክ እንዳይጠቀሙ ማድረጉን ጠቁመው፤ ባለፈው ዓመት በዘመናዊ መንገድ ካለሙት አንድ ተኩል ሄክታር መሬት 28 ኩንታል የቢራ ገብስ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ለሲሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል ምርታቸውን በ60 ሺህ ብር ሽጠው ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ ዘንድሮም ካለሙት ሁለት ሄክታር ከሚበልጥ መሬት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር መሃመድ ሰይድ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ድንችና ሽንኩርት ያመርቱ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ በዘመናዊ መንገድ አንድ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡

“እየተደረገልኝ ባለው የባለሙያ ድጋፍ ራሴን ከኮሮና ቫይረስ ጠብቄ ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተንከባከብኩ ነው" ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ተካፋይ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም