በትግራይ ኮሮናን ለመከላከል የውሀ አቅርቦትን የማሟላት ስራ ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ኮሮናን ለመከላከል የውሀ አቅርቦትን የማሟላት ስራ ተከናወነ
መቀሌ ፣ ሚያዚያ 24/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከ59 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የውሃ አቅርቦት የማሟላት ስራ መከናወኑን የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
ለመጠጥ ውሃ እና ለግል ንፅህና መጠበቂያ አገልግሎት የሚውል የውሃ አቅርቦት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲኖር ለማስቻል ጥረት መደረጉን የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ ኃላፊና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል።
በዚህም በተለያዩ ወቅቶች ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጭ ከነበሩት 547 የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓዶች መካከል 363 የሚሆኑት በተያዘው ወር ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም 159 አዳዲስ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው ለአገልግሎት በማብቃት 160 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
ጥገና ለተደረገላቸውና ለተቆፈሩት አዳዲስ የውሃ ጉድጓዶች ከክልሉ መንግስትና በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት 59 ሚሊዮን 400ሺህ ብር ወጪ መደረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈርና መስመር ለመዘርጋት የመሬት አቀማመጣቸው በማይመቹ አካባቢዎች ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በ52 የውሃ ቦቴ ተሽከርካሪዎች ውሃ እየቀረበ ነው።
በዚህም እስካሁን 150 ሺህ የሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች የአቅርቦቱ ተጠቃሚመሆናቸውን ገልጸዋል።
በየዞኖቹ ለሚከሰቱት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር የሚከታተልና ጥገና የሚያደርግ ክፍል ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ከተጠቃሚዎች መካከል የአላማጣ ከተማ ነዋሪ አቶ መሓሪ ገብረሚካኤል በሰጡት አስተያየት የነበረባቸውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ በመፈታቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የውሃ አቅርቦት በመሟላቱም ኮሮናን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች በሚሰጣቸው ምክር የግል ንጽህናቸውን በመጠበቅ ጥንቃቄ እያዳረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከአራት ወራት በፊት በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ የቆየው የአካባቢያቸው የውሃ ጉድጓድ ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱን የተናገሩት ደግሞ የላእላይ አድያቦ ወረዳ አርሶ አደር አየለ ብርሃነ ናቸው።
ጥቅም ላይ በዋለው የውሃ ጉድጓድም የውሃ አቅርቦት ችግራቸው መቃለሉን አስረድተዋል።