ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ ድጋፍ ለሚሹ ሦስት ማህበራት የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን አበረከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24/2012(ኢዜአ)የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ድጋፍ ለሚሹ ሦስት ማህበራት የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን በስጦታ አበረከተ።

ድጋፉ የኮሮናቫይረስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን አገራዊ ጥረት ለማገዝ ታስቦ የተደረገ መሆኑንም ባለስልጣኑ ገልጿል።

በባለስልጣኑ ዛሬ ድጋፍ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማህበር፣ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር እና ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማህበር ናቸው።

ቁሳቁሱን ለማህበራቱ ያስረከቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ እንደገለጹት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለአስቸጋሪ ሕይወት ከሚጋለጡ ዜጎች መካከል መስማት የተሳናቸው፣ ዓይነስውራንና የአዕምሮ ሕሙማን በዋናነት ይጠቀሳሉ።

"እነዚህ አካላት በአቅማቸው ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በእጅጉ እየተጎዱና የእለት ጉርሳቸውን እንኳ መሸፈን እያቃታቸው ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል" ብለዋል።

በዚህም ባለስልጣኑ ለማህበራቱ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማበርከቱን ነው የገለጹት።

ባለስልጣኑ ቁሶቹን ያበረከተው በራሱና ከተለያዩ አጋዥ አካላት ጋር በመተባበር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ድጋፉ በቂ ባይሆንም የወቅቱን አስከፊነት በመገንዘብ የመረዳዳት ባህልን ለማዳበር በሚል የተደረገ ነው።

ባለስልጣኑ በቀጣይም ለሌሎች አካላት መሰል ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልጸው፣ አሁን በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተስተዋለ ያለው የመደጋገፍና የመረዳዳት ልምድ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው ማህበራት በበኩላቸው በዚህ አስከፊ ወቅት የተደረገላቸው ድጋፍ አባሎቻቸውን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ወቅቱ ድጋፍ የሚሹ ማህበራት የሁሉንም ማህበረሰብ ተሳትፎና እገዛ የሚሹበት በመሆኑ ይህንን እርዳታ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ህብረተሰቡ በቅንነት እያደረገላቸው ያለው እገዛ የኢትዮጵያውያንን የቆየ የመረዳዳትና የመተጋገዝ እሴት ያሳየ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም