ቀጥታ፡

ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚውል "ንጋት" የተሰኘ የሙዚቃ አልበም ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2012( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ኅብረት ለኮቪድ-19 መከላከል ሥራ የሚውል "ንጋት" የተሰኘ የሙዚቃ አልበም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አበረከተ።

ኅብረተሰቡ አልበሙን በመግዛት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን እንዲያግዝም ጥሪ ቀርቧል።
 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ በነጻ የተበረከተውን አልበም መርቀው ተቀብለዋል።

የተበረከተው አልበም የተለያዩ አንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን የተሳተፉበት 15 ሙዚቃዎችን የያዘ ሲሆን በይዘቱም የተለያዩ አገራዊ እሴቶች የተንጸባረቁበት ነው።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ኅብረት ፕሬዚዳንት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ እንዳለው፣ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች በኮፒ ራይተና በሌሎች ጉዳዮች በርካታ ፈተናዎች አሉባቸው።

ይሁን እንጂ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በሙያቸው ለማገዝ "ንጋት" የተሰኘ የሙዚቃ አልበም ሰርተው ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከባቸውን ገልጿል።

አልበሙ በወረርሽኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳትና የመንግስትን ጥረት ለማገዝ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ኅብረቱ ላበረከተው አስተዋዕኦ ምስጋና አቅርበዋል።

"የከተማ አስተዳደሩም 'ንጋት' ከተሰኘው የሙዚቃ አልበም ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ዓላማ እንዲውል ያደርጋል" ብለዋል።

"እኛ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሙን በጋራ በመሆን ችግሮችን እያሸነፍን ከዚህ ደርሰናል" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ኅብረት ዛሬ ያደረገው አስተዋጽኦ አንድ ላይ ከመቆም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ማሳያ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

"የከተማ አስተዳደሩ የኪነ ጥበብ ዘርፉ እንዲያድግና እንዲጎለብት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል" ሲሉም ምክትል ከንቲባው ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ኅብረት ፕሬዚዳንትም ኅብረተሰቡ አልበሙን በመግዛት የተቸገሩ ወገኖችን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

"ንጋት" ከተሰኘው የሙዚቃ አልበም በኋላ ሌሎች የሙዚቃ አልበሞች በተለያዩ አርቲስቶች በጋራ እንደሚሰሩም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም