አዋጁን የተላለፉ ከ8ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
አዋጁን የተላለፉ ከ8ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጡ
ባህርዳር፣ ሚያዚያ 24/2012 (ኤዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈው የተገኙ ከ8ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አሰታወቀ።
የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት መቆጣጠርና መከታተል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ ለኢዜአ እንደገለጹት አሽከርካሪዎቹ የተቀጡት የአዋጁን ድንጋጌዎች ጥሰው በመገኘታቸው ነው።
በዚህም ከተፈቀደላቸው በላይ ሰውና እቃ ሲጭኑ ፣ ተሽከርካሪዎችን ሳኒታይዘር ሳይረጩና ሌሎችን ክልከላዎች ጥሰው የተገኙ 8 ሺህ 840 አሽከርካሪዎች ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ መቀጣታቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም 1 ሺህ 466 አሽከርካሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በየከተሞቹ ስለቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች በተሽከርካሪ የታገዘ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተሰራ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳልመጣ ኮማንደሩ ጠቁመዋል።
በቀጣይ በየደረጃው የተዋቀረው የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አዋጁን በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ለማስፈፀም የተጠናከረ ስራ እንደሚያካሄድ ገልጸዋል።