የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ማህበረሰቡ እያሳየ ያለው መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ማህበረሰቡ እያሳየ ያለው መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት ማህበረሰቡ እያሳየ ያለው መዘናጋትና ቸልተኝነት አሳሳቢ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።
የህክምና ባለሙያዎች ከፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ሰዎች በበዙባቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፈዋል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በመዘንጋት በአንድ አካባቢ መሰባሰብ፣ በትራንስፖርትና በንግድ ቦታዎች በመጠጋጋትና ምንም አይነት ጥንቃቄ ሳያደርግ ሲገበያይ እየተስተዋለ ነው።
ማህበረሰቡ ርቀቱን ጠብቆ፣ የአፍና አፍንጫ ማስክ አድርጎ እንዲሁም እጅ መታጠብን በማዘውተር ካልተንቀሳቀሰ እንደ አገር አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል ሲሉ ሃኪሞቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አንዳንድ ግለሰቦች ሳይንሳዊ መሰረት በሌለው’’የኮሮናቫይረስ ስርጭት ቆሟል" በማለት በሚያሰራጩት የሃሰት ወሬም ማህበረሰቡ እንዳይዘናጋ አሳስበዋል።
የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጤና ቢሮ ሃላፊ እንጋ እርቀታ እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የወጣው አዋጅ በአብዛኛው እየተተገበረ አይደለም።
አደባባይ በመውጣት የጥንቃቄ እና ምክር ተግባር ያከናወኑት የህከምና ባለሙያዎችና አጋሮች፤ ህብረተሰቡ ለቫይረሱ አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች እንዲታቀብ ለማሳሰብ ነው ብለዋል።
ቫይረሱ በጣም አደገኛና ተላላፊ በመሆኑ የግድ ካልሆነ መስተቀር ሰዎች ከቤት ባለመውጣት ቢከላከሉ ይመረጣልም ብለዋል።
ይህ ካልሆነ ደግሞ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በውሃና በሳሙና በአግባቡ መታጠብና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ መንገዶችን በመከተል መከላከል እንደሚገባ ሃኪሞቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የፖሊስ አባላትም ህግን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ነዋሪው የለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮሮናቫይረስ የኢትዮጵያ አሁናዊ መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን በቫይረሱ 133 ሰዎች ሲያዙ 69ኙ ከህመሙ አገግመዋል።
ቀሪዎቹ ደግሞ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
ዓለም አቀፍ መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ከ3 ሚሊዮን 359 ሺህ በላይ የዓለም ህዝቦች ለኮሮናቫይረስ ህመም ተዳርገዋል።
በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ 239 ሺህ የዓለም ህዝቦችም ህይወታቸውን ማጣታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመለክታል።