ቀጥታ፡

ለባህል እና ኪነ ጥበብ እድገት የባህል ማዕከላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ  ሰኔ 27/2010 ለአንድ አገር ህዝቦች የባህል እና የኪነ ጥበብ እድገት የባህል ማዕከላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል ''የባህል ማዕከላት ሚና ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ'' እና ''በኢትዮጵያዊነት ፊልሞች ውስጥ ኢትጵያዊነት አለን?'' በሚል አብይ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሽመልስ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፤ የአንድ አገር የባህል ማዕከል የህዝቦቿ የባህላቸው ውጤት በመሆናቸው  በተለይም እንደ እኛ አገር ብዝሃ ባህል ያለን ህዝቦች ስንሆን የባህል ማዕከላት መኖር ሚና ላቅ ያለ ነው። በመሆኑም በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዲህ ያሉ ውይይቶችን ከባለድርሻ አካላትጋር ሆኖ መወያየቱ ጠቃሚ ነው ብለዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፤ የአገር ግንባታ በብዙ አስተሳሰቦች፣ እውቀቶችና ጥረቶች የሚመጣ  ነው። በዛሬው እለትም በኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል አዘጋጅነት የሚደረገው ይህ ውይይት እንደ ፌዴራል ተቋም አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ለመስራት የጀመርነውን እንቅስቃሴ ማሳያ ነው ብለዋል። ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስዕል ትምህርት ክፍል የተገኙ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅረበዋል። እንደ ጥናታቸውም የባህል ማዕከላት የሰው ልጅ የፈጠራ ጥበባት መለማመጃ ቦታዎች በመሆናቸው፤ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ዜጋ ሊጠቀምባቸው መቻል አለበት። ይህም ተግባራዊ መሆን ሲጀምርና የባህል ማዕከሉ በመደበኛነት ሁሉንም ማገልገል ሲጀምር የሚጠበቀውን ማየት እንጀምራለን ብለዋል። በነገው እለትም ''በኢትዮጵያዊነት ፊልም ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አለን?'' በሚል ርዕስ የሚካሄድ ውይይት የሚቀጥል ሲሆን በአገሪቷ እየተመረቱ ያሉት ፊልሞች ከኢትዮጵያዊነት ይዘታቸው አኳያ ሰፊ ማብራሪያዎች እየተነሱ የሚወያዩበት ይሆናል። የወደ ፊት አቅጣጫዎቹም ምን መምሰል እንዳለበት እንደሚመክሩበት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም