ቀጥታ፡

የኮሮናቫይረስን ለሚያክሙ ባለሙያዎች የማርና በግ ስጦታ ተበረከተላቸው

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2012 (ኢዜአ)የኮሮናቫይረስን በማከም ስራ ላይ ለተሰማሩ ሃኪሞችና ባለሙያዎች ከከፋ ዞን የአገር ሽማግሌዎች የማርና በግ ስጦታ ተበረከተላቸው።

የከፋ ዞን አስተዳደርና የአገር ሽማግሌዎች በአዲስ አበባ ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ተገኝተው የኮሮናቫይረስን በማከም ስራ ለተጠመዱ ባለሙያዎች ግምቱ ከ100 ሺህ ብር በላይ የሆነ የማርና በግ ስጦታ ዛሬ አስረክበዋል።

የከፋ ዞን የአገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ አድማሱ አቱሞ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሀኪሞችና ባለሙያዎች እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይሳሱ ለኅብረሰተባቸው እያዋሉ ነው።

''በዚህ አበርክቷቸውም ፈጣሪ ከጎናቸው እንዲሆን እንመኛለን፣ ለሞራል እንዲሆናቸው የበረከት ምሳሌ የሆኑትን የማርና በግ ስጦታ አበርክተናል'' ብለዋል።

ሀኪሞችና ባለሙያዎች ጥረታቸው ለፍሬ በቅቶ ታማሚዎች አገግመው ለቤታቸው እንዲበቁ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው ከከፋ ዞን አባቶች፣ ወጣቶችና የዞኑ አስተዳደር ስለቀረበላቸው ስጦታና መልካም ምኞት ምስጋና አቅርበዋል።

"እኛም ለእናንተ መልዕክት አለን" ያሉት ዶክተር ያሬድ፤ ''ለእኛ ያላችሁን ፍቅርና አክብሮት ራሳችሁን ከወረርሽኙ በመጠበቅ ልታሳዩን ይገባል'' ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ''የከፋ ዞን የአገር ሽማግሌዎች ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎችም አካባቢዎች አርዓያ የሚሆን ነው'' ብለዋል።

ከእነዚህ የከፋ ዞን ደግ አድራጊዎች በመማር በሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች ያሉትም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኅብረተሰቡ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግም ባለፈ ራሱን ከአካላዊ ንክኪ በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም