በህገ ወጥ መንገድ ከውጭ የገቡ 73 ዜጎች በማቆያ እንዲሆኑ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ መንገድ ከውጭ የገቡ 73 ዜጎች በማቆያ እንዲሆኑ ተደረገ
መተማ፤ሚያዝያ 23/2012( ኢዜአ) በህገ ወጥ መንገድ በምዕራብ ጎንደር ዞን በኩል ከውጭ የገቡ 73 ዜጎች ከኮሮና ለመጠንቀቅ በማቆያ እንዲሆኑ መደረጉን የዞኑ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
የግብረ-ኃይሉ ፀሓፊና የማህበራዊ ጉዳዮች ልማት መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ለኢዜአ እንደገለፁት ዞኑ ከሱዳን ጋር በድንበር የሚዋሰን በመሆኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጠንካራ ክትትል እየተደረገ ነው።
በዚህም ባለፉት ሶስት ቀናት ግብረ ኃይሉ በሚያስተላለፈው አቅጣጫ መሰረት የጸጥታ ኃይሉ ባደረገው ክትትል 73 ኢትዮጵያዊያን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር መግባታቸውን ተናግረዋል።
ዜጎቹ በመተማ ዮሃንስ ከተማ የሙቀት ልኬት ተደርጎላቸው በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማ በተዘጋጀ የለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት እንዲቆዩ መግባታቸውን ሲስተር ክሽን አስታውቀዋል።
በተጨማሪ ከመተማ ዮሃንስ ጤና ጣቢያ እና ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር አስተዳደር ጋር በመተባበር የወባ ምርመራ እንደሚደረግላቸውም አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም የፀጥታ ኃይሉ በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ዜጎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ ጠንካራ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር አስተዳደር የመተማ መውጫና መግቢያ ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ መለሰ ማስሬ በበኩላቸው ከውጭ የገቡት ዜጎችን ለጥንቃቄ እንዲረዳ የጤንነት ሁኔታ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር የነበሩበትን ቦታና የሚሄዱበትን አካባቢ በመመዝገብ መረጃ እንደሚያዝና የሚመለከተው አካል እንዲያውቀው የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።
የልየታ ስራው ቦታ የተሟላ መገልገያ ምግብና ቁሳቁስ ባለመኖሩ የሚመለከተው አካል ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ከ2ሺህ 600 በላይ ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የሙቀት ልኬት ስራ በማከናወን በማቆያ ጤንነታቸውን በማረጋገጥ እንዲያልፉ መደረጉም ተመልክቷል።