ቀጥታ፡

ሰራተኞች በህገ ወጥ መንገድ ከስራ እየተሰናበቱና እየታገዱ ነው ... ኮንፌድሬሽኑ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2012( ኢዜአ) ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ ሰራተኞች በህገ-ወጥ መንገድ ከስራ ገበታቸው እየታገዱና እየተሰናበቱ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ የአለም አቀፍ የሰራተኞች ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልክት  ኢትዮጵያ ከገጠማት የኮሮናቫይረስ ሁኔታ አንጻር ሰራተኞች የመብትና ጥቅም መጓደል ጥያቄን የሚያስተጋቡበት ወቅት አለመሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ አሰሪዎች በህገወጥ መንገድ ሰራተኛን  ከስራ እያሰናበቱና እያገዱ መሆኑን ነው ብለዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ አሰሪዎች የሰራተኛ ማህበራትንም እያፈረሱ ይገኛሉ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ፍርድ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ቅሬታቸውን አቅርበው መፍትሄ የሚያገኙበት ሁኔታ ባለመኖሩ ሰራተኞች ችግር ውስጥ እንደገቡም ገልጸዋል።

በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስፈጸም ሃላፊነት የተሰጣቸው የመንግስት አካላት አስቸኳይ የማስተካካያ እርምጃ እንዲወስዱ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

መንግስት በስራ ቦታና ከስራ ውጪ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በማካተት ማውጣቱን ገልጸው፤  የተወሰኑ አሰሪዎችና ባለሃብቶች በሽታውን ለመከላከልና በስራ ቦታ መውሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች እየወሰዱ ባለመሆኑ የሰራተኛ የስራ ዋስትና ላይ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነም አመላክተዋል።

 የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መላው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ከመንግስትና ከአሰሪዎች ጋር በመተባበር እያደረጉ ያለውን ጥረት እንዲቀጥሉም  አቶ ካሳሁን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም