ቀጥታ፡

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እየተሰራ ያለውን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ በሁሉም ዘርፍ እየተሰራ ያለውን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።

ወረርሽኙን መንግስት ብቻውን መከላከል የማይችል በመሆኑ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በሽታውን እንዲከላከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
 

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋመው ብሄራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎች ሲሰሩ የቆዩ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ኮሚቴው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በትራንስፖርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በውጪ ጉዳይ ላይ እና በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ካለው የድጋፍ አሰባሰብ ጋር ያሉ ስራዎችን በሚመለከት ነው ሪፖርት ያደረገው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመንግስት በኩል ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እና በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው ለውጥ የመጣ ቢሆንም አሁንም በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ለአብነትም የገበያ እና የትራንስፖርት አጠቃቀም ላይ ያለውን የህዝብ ጭንቅንቅ በማንሳት በሽታው የከፋ አደጋ ሳያስከትል በፍጥነት ማረምና ማስተካከል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የላቦራቶሪ መመርመሪያ አቅምን ማሳደግ በመቻሉ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች 24 ላብራቶሪ እና 27 መመርመሪያ መሳሪያ እንዳለም ጠቁመዋል።

በቤት ለቤት ልየታ እስካሁን 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶች መጎብኘታቸውን እና በቤት ለቤት ልየታ አዲስ አበባ፣ ትግራይ እና አሮሚያ ክልሎች ጥሩ እንደፈጸሙ በሪፖርታቸው አቅርበዋል።

እስከ ዛሬ ድርስ 133 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ  መገኘታቸው እና ከእነዚህ ውስጥ 66 ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸውንም ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ወረሽኙን ለመከላከል 15 ቢሊዮን ብር የበጀት ሽግሽግ እንደተደረገና በአጠቃላይ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመደበኛ የነበረው 15 ሚሊዮን ተረጂ በኮቪድ-19 ምክንያት 15 ሚሊዮን ተጨምሮበት 30 ሚሊዮን ህዝብ እርዳታ የሚያስፈልገው በመሆኑ ይሄንን ችግር ለመፍታት በአዲስ አበባና በክልሎች የምግብ ባንክ መቋቋሙን ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የሀብት ማሰባሰብ ንዑስ ኮሚቴ በክልል እና በፌዴራል እስካሁን በሀብት ማሰባሰብ ረገድ የሰራቸውን ስራዎች አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር  መድረሱን እና 40 ሚሊዮን የሚሆን ደግሞ በአይነት መገኘቱን ተናግረው የምግብ ክምችት እና ስርጭት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወለደ ገብረማሪያም በበኩላቸው በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ወደ አዲስ አበባ በቀን በአማካኝ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር 30 ሰው ብቻ መሆናቸውን እና በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት የሚገቡ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።

አየር መንገዱ በጭነት አገልግሎት ጥሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በአትክልትና አበባ እንዲሁም በስጋ ምርቶች ላይ የትራንስፖርት ፍላጎት መጨመሩ ለአየር መንገዱ ገቢ እያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የእያንዳንዱን ዘርፍ የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ካደመጡ በኋላ በሰጡት የስራ መመሪያ ኮቪድ-19 በመከላከል ረገድ በሁሉም ዘርፍ እየተሰራ ያለው ውጤታማ ስራ ሳያዘናጋ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከጤና አንፃር ከኮቪድ-19 ውጪ ያሉ በሽታዎችንም በእኩል ሁኔታ የሚሰሩበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ እና የተቋማት ምላሽ የመስጠት አቅምን መፈተሽ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ከሌሎች አገሮች አንፃር ይሄ ነው የሚባል ድጋፍ ሳይደረግለት ራሱን ችሎ መቆሙን ያቀደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል መሆኗን ያረጋገጠ መሆኑንም ገልፀዋል።

''አየር መንገዱ አገሪቱ በክፉ ጊዜ የምትጠቀምበት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ አቅሙን አጎልብቶ እየሰራ ያለውን ውጤታማ ስራ ማጠናከር ይገባዋል'' ብለዋል።

''በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የመዘናጋት ሁኔታዎች ይስተዋላል'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በትክክል ማድረስ እንደሚገባና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን ቆሞ ወረርሽኙን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

ህግ አስከባሪዎች የወጣውን አዋጅ በትክክል ማስተግበር እንዳለባቸውና ዜጎችም ለህግ ተገዥ እንዲሆኑ በማሳሰብ ጥቃቱን መንግስት ብቻውን ሆኖ መመከት የሚችል ባለመሆኑ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በሽታውን እንዲከላከል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በትራንስፖርት በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት የመንግስት ተቋማት ድጋፍ ማድረግ እንዳባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም