ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የቅንጅት ስራዎች መጠናከር አለበት ተባለ

ሐረር (ኢዜአ) ሚያዚያ 23 / 2012 በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማጎልበት የቅንጅት ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰመስተዳድር አስገነዘቡ፡፡
በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እየተደረጉ ያሉት ጥረቶችን በአብይ ኮሚቴው ተገምግሟል ።

የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ወርዲ አብዱላሂ በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ግንዛቤን በመፍጠር፣የለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማእከላት በማዘጋጀትና  በሀብት አሰባሰብ  ረገድ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በተለይ በለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት፣በማረሚያ ቤቶችና ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የውሃ እጥረት እንዳይከሰት ውጤታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ በስድስቱም መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይና ቤት ለቤት እየተከናወነ የሚገኘው ሙቀት የመለካት  ስራ አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ  ይቀጥላል ብለዋል።

በፌዴራልና በክልሉ ከትራንስፖርት፣ከግብይት፣ከእምነት ስፍራዎችና በሌሎች ላይ  የወጡ አዋጆችንና ክልከላዎችን ከማስተግበር አኳያ የተሻለ ስራ ቢከናወንም ፖሊስ፣አቃቢ ህግና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ የቅንጅት ስራዎችን ማጠናከር   ይገባል ብለዋል።

በገበያ ስፍራዎች ላይ ርቀትን ጠብቆ ከመገልገል አንጻር አሁንም ቸልተኝነትና የአመለካከት ክፍተት እንዳለ ጠቁመዋል ።

የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ የትብብር ስራዎችን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ቫይረሱን ከመከላከል አኳያ  በወረዳዎች  መካከል ወጥ የሆነ ስራ መሰራት ይገባል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ መሰረታዊ ፍጆታዎችን ከማሟላትና በጤና ባለሙያዎች  የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ከማስተግበር አኳያ አብይ ኮሚቴው የተጠናከረ ስራ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ሐላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል  አቶ ኢብሳ አብራሂም በበኩላቸው በክልሉ ቫይረሱን ለመከላከል እስከ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ድረስ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል ።ሰ

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ 6ቱም መግቢያና መውጪያ በሮች ከ220 ሺህ በላይ ሰዎችን የሙቀት መጠናቸው የተለካ ሲሆን በቤት ለቤት አሰሳም ከ7 ሺህ  በላይ መኖርያ ቤቶች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም