ቀጥታ፡

አዋጁን ተላልፈው ድግስ ያዘጋጁና በተሽከርካሪ ከልክ በላይ ያሳፈሩ ግለሰቦች ተቀጡ

ሚያዚያ 23/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተላልፈው የተለያየ ድግስ ያዘጋጁና በተሽከርካሪ ከልክ በላይ ሰዎችን አሳፍረው የተገኙ ግለሰቦች መቀጣታቸውን ፖለስ አስታወቀ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የፖሊስ መምሪያው የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ራሄል አብረሃም እንዳሉት የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌዎች በመጣስ  የደገሱ 978 ግለሰቦች ተቀጥተዋል።

ከቅጣቱም መካከል ተዘጋጅተው የነበሩ የ750 ሰርጎች፣ የ80 ተዝካሮችና ስምንት የቁርባን ድግሶች እንዲቋረጡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ግብረ ኃይሉ  እስከ ቀበሌ ድረስ ግንዛቤ ፈጥሮ ባደረገው  ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ድርጊቱን ማስቆም ተችሏል።

እስካሁንም ስድስት ደጋሾች ከታዳሚዎቻቸው ጋር እስከ አራት ዓመት  በሚደርስ እስራትና እስከ  አንድ ሺህ ብር መቀጣታቸውን አስታውቀዋል።

ይህም ሆኖ አሁንም አዋጁን በመጣስ የደገሱ 140 ግለሰቦችን በመለየት ለህግ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ህግን በማስከበር የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ግብረ-ሃይሉ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ኮማንደሯ አብራርተዋል።

በተመሳሳይ በሰቆጣ ከተማ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሊፈፀም የነበረ 12 የሰርግ ስነ ስርዓቶች እንዲቋረጡ መደረጉን የከተማው ፖሊስ የጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ክፍል ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል  ረዳት ኢንስፔክተር አበራ አግኝቸው ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በአዋጅ የተጣሉ እገዳዎችን ተላልፈው የተገኙ አካላትን  በመጠቆም እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ በድብቅ ሊፈፀም የሚችልን የሰርግ ድግሶችን ለመቆጣጠርም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ  ከተፈቀደላቸው የሰዎች ቁጥር በላይ ጭነው ሲያጓጉዙ የተገኙ 25 አሽከርካሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በገንዘብና በእስራት መቀጣታቸውን የከተማው ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል  ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ አስታውቀዋል።

አሽከርካሪዎቹ የአዋጁን ድንጋጌዎች መተላለፋቸው በማስረጃ በመረጋገጡ 23 አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው በ6ሺ ብር እንዲቀጡ ተደርጓል።

የባጃጅ እና "አባዱላ" የተባለ የህዝብ ማመላለሻ  አሽከርካሪዎች እስከ አንድ ዓመት እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ እንዳሉት ደንብ በሚጥሱ አካላት ላይ ፖሊስ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለህግ የማቅረቡን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ህብረሰቡም የህግ ጥሰቶች ሲፈጸሙ በሚመለከትበት ወቅት ፈጥኖ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም