በኮቪድ-19 ምክንያት በሰራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጪ የስራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊደረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኮቪድ-19 ምክንያት በሰራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጪ የስራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊደረግ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 23/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት በሠራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የሥራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜና በዓለም ለ131ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን (ሜይዴይ) አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የስራ ቦታና ሰራተኛው ለወረርሽኙ ያለውን ከፍተኛ ተጋላጭነት በተመለከተ በመልዕክታቸው አንስተዋል።
የዘንድሮው ሜይዴይ የሚከበረው የኮሮናቫይረስ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ዓለምን በወረረበትና በሠው ልጅ ላይ አደጋ በደቀነበት ጊዜ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል አገሮች ጥረት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በሚደረገው ትግል የተለያየ መስዋትነት እየጠየቀ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያም የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ''በመንግስት፣ በአሠሪና ሠራተኛ አካላት ምክክር የወጣው “የኮቪድ-19 የሥራ ቦታ ምላሽ የሦስትዮሽ ኘሮቶኮል” እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሥራ ቦታ ላይ የጣለውን ኃላፊነት መተግበር ያስፈልጋል'' ብለዋል።
በሠራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የሥራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተር ኤርጎጌ ''ተባብሮና ተደጋግፎ የመሻገር ጉዟችን ቀዳሚው ትኩረት ነው'' ብለዋል፡፡
ወቅቱ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ደህንነት መቆምን ና በአንድነት መሰለፍን የሚጠይቅበት ጊዜ በመሆኑ ለሰራተኛው መብት መከበር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል ሰራተኛው ራሱን እየጠበቀና ሌላውን እየታደገ በአሸናፊነት ለመሻገር በተደራጀና በተቀናጀ አቅም አንድ ላይ መስራት እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።
ገለጻ፤ የወረርሽኙን የመከላከያ መንገዶችንና የጥንቃቄ ደረጃዎችን በመከተል ሠራተኛው መጠበቅ እንደሚገባም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ሜይዴይ የዓለም ላብ አደሮች ያለፉበትን የትግል ውጣውረድና የጨበጡትን ድል የሚያስቡበትና መጪውን ዘመን አሻግረው የሚያስተውሉበት ቀን መሆኑንም አውስተዋል።
የዓለም ሠራተኞች አካልና የትግል አጋር የሆነው የኢትዮጵያ ሠራተኛም ከዓለም አቀፍ የላብ አደሮች የትግል ጉዞ የተለየ ታሪክ እንደሌለው ያስታወሱት ዶክተር ኤርጎጌ፤ ''በኢትዮጵያ የማምረቻው ዘርፍ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበር ያደረጉት መራር ትግል በደማቅ ቀለም ተፅፏል'' ብለዋል።
በተደረገው ትግልም ሠራተኛው በሥራ ቦታ ክብርና ደህንነቱ፣ መብትና ጥቅሙ እንዲከበር መንገድ የከፈተ መሆኑንም አንስተዋል።
ሜይዴይ ሲከበርም ለሰራተኛው መብት የታገሉትን ሠራተኞችና የሠራተኛ መሪዎች ክብር እንደሚገባቸው ገልጸው፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታትም ተመሳሳይ ገድል እንዲፈጽሙ ጠይቀዋል።
''ሠራተኛው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ የላቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን እየታገለ፤ የከፈለው መስዋትነት ሜይዴይ በተከበረ ቁጥር ሲዘከር ይኖራል'' ብለዋል፡፡