በአማራና ደቡብ ክልሎች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ተፈረሙ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራና ደቡብ ክልሎች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ተፈረሙ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአማራና ደቡብ ክልሎች የመንገድ ፕሮጀክቶችን ወደ አስፓልት ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈረመ። መንገዶቹ በአጠቃላይ 111 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍኑ ሲሆን ለግንባታቸው ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረብርሃን አንኮበር መንገድ 42 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን መንገዱ ከዚህ ቀደም ከስድስት እስከ ሰባት ሜትር ስፋት ባለው የጠጠር መንገድ ደረጃ የነበረ መሆኑ ተገልጿል። ለመንገዱ ግንባታም ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። የመንገዱ ግንባታ ስፋት በከተሞች የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 17 ሜትር ሲሆን በገጠር በግራና ቀኝ 1 ነጥብ 5 ሜትር የመንገድ ትከሻን ጨምር 10 ሜትርና የውሃ መውረጃ ቱቦ ስራዎችንም የሚያካትት ነው ተብሏል። ግንባታውን የሚያከናውነው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የተሰኘ አገር በቀል የስራ ተቋራጭ ሲሆን የቁጥጥርና የማማከር ስራውን ደግሞ የአገር በቀሉ ኮር የተባለ አማካሪ ድርጅት ነው። ሌላኛው በደቡብ ክልል የሚገነባው የአብሎ ደርሚ መንገድ 69 ኪሎሜትር የሚሸፍን ሲሆን ለግንባታው ከ893 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያስፈልግ ታውቋል። መንገዱ ከዚህ ቀደም ደረጃውን ባልጠበቀ የጠጠር መንገድ ደረጃ የነበረ ሲሆን አሁን ግንባታው በከተሞች የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 19 ሜትር በገጠር ደግሞ ስምንት ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚሰራ ነው። ግንባታውን የሚያከናውነው ክሮስ ላንድ ኮንስትራክሽን የተሰኘ አገር በቀል የስራ ተቋራጭ ሲሆን የቁጥጥርና የማማከር ስራውን የሚያከናውነውን ድርጅት ለመምረጥ በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል። የሁለቱም መንገዶች ግንባታ ካላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር በአስፓልት ደረጃ እንዲገነቡ ታቅዶ የውል ስምምነት መፈረሙን ነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያስታወቀው።