ቀጥታ፡

ለሰፋፊ እርሻ ልማት ዝግጅት የጉልበት ሰራተኛ እጥረት አጋጥሟል

ሚያዚያ 22/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደርና በትግራይ ደቡባዊ ዞን የኮሮና ቫይረስን በመከላከል የልማት ስራውን ለማስቀጠል የተያዘው አቅድ በጉልበት ሰራተኞች እጥረት እንዳይደናቀፍ ስጋት ማሳደሩ ተገለፀ ።

የምእራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት በልሁ ለኢዜአ  እንደተናገሩት  የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎን ለጎን የመኽር እርሻ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በባለሃብቱም ሆነ በአርሶ አደሮች በተለያዩ ሰብሎች የሚለማ 200 ሺህ  ሄክታር ማሳ የፅዳት ስራ ማከናወን ያስፈልገዋል።

ከየካቲት ወር ጀምሮ 20 ሺህ የጉልበት ሰራተኞችን በማሰማራት 70 ሺህ ሄክታር መሬት  በማፅዳት ዝግጅት ማድረግ እንደተቻለም ገልፀዋል።

ቀሪው 130 ሺህ ሄክታር መሬት በግንቦት ወር መጠናቀቅ ያለበት በመሆኑ ለፅዳት ስራው  ከ50 ሺህ ያላነሰ የጉልበት ሰራተኛ ማስፈለጉን አብራርተዋል።

በከተሞች የሚገኙ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ወደ እርሻ ቦታዎቹ በመሰማራት የስራ እጥነት  ችግራቸውን ከመፍታት ባለፈ የግብርና ስራውን ማገዝ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የጉልበት ሰራተኞቹ ወደ ልማት ቦታው በሚሄዱበት ወቅትም ኮሮናን መከላከል በሚያስችል አግባብ ከባለሃብቱ ጋር በመነጋገር የትራንስፖርት አቅርቦት የሚመቻች  መሆኑንም አስታውቀዋል።

አርሶ አደሩና ባለሃብቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎን ለጎን የግብርና ስራው  ላይም ሰፊ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የመምሪያ ሃላፊው አሳስበዋል።

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ድርማጋ የእርሻ ልማት 256 ሄክታር መሬት እያለሙ  የሚገኙት ባለሃብት አቶ ተካ አለሙ በሰጡት አስተያየት የማሳ ማፅዳት ሥራ ወቅቱን  ጠብቆ ካልተሰራ ምርትና ምርታማነቱን ይጎዳል፡፡

ያልፀዳ ማሳ ለትራክተርም ሆነ ለበሬ እርሻ የማይመች ከመሆኑም ባለፈ ሰብሉ በአረም  እንዲጠፋ ያደርጋል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል ።

እስካሁን 30 የጉልበት ሰራተኞችን በማሳተፍ ከ40 ሄክታር ያልበለጠ ማሳ ማፅዳት እንደቻሉ የገለፁት ባለሃብቱ የዘር ወቅት ከመድረሱ በፊት ቀሪውን ሄክታር መሬት  ለማፅዳትም  70 የጉልበት ሰራተኞች እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

በመተማ ወረዳ ደለሎ የእርሻ ልማት ባለሃብት አቶ አበራ በላይ በበኩላቸው ካላቸው  140 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ50 ሄክታር በላይ ማሳቸውን ማፅዳት እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዞኑ በዚህ አመት በባለሃብቱ ብቻ 124 ሺህ ሄክታር መሬት ሰሊጥን ጨምሮ በሌሎች  ሰብሎች እንደሚለማ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ራያ አዘቦ ወረዳ ቫይረሱ በፈጠረው ስጋት ምክንያት የጉልበት ሰራተኞች እጥረት ማጋጠሙን በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ገልፀዋል ።

በወረዳው አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ወደ ውጪ የሚልከው ''ቫል ቬርዴ" የተባለው የስፔን ካምፓኒ በቫይረሱ ስጋት ምክንያት የጉልበት ሰራተኞች እጥረት አጋጥሞኛል ብሏል ።

የካምፓኒው ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሄም አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው በመስኖ ያለሙት ምርት  በሰራተኞች እጥረት ምክንያት መሰብሰብ አልተቻለም።

ቫይረሱ በፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት በእርሻ ስራው የነበሩ ከ2 ሺህ በላይ ሰራተኞች በራሳቸው ፍቃድ  ለቀው መሔዳቸውን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል ።

በአሁኑ ወቅት በካምፓኒው የቀሩት ሰራተኞች ቁጥር 719 ብቻ መሆናቸውን ገልፀው ልማቱን ለማካሔድ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ለመቅጠር እንደሚፈልጉ አስረድተዋል ።

ከአሁን በፊት በቀን እስከ 20 ቶን ድረስ "አስባረገስ" የተባለ የአትክልት ምርት ይሰበሰብ እንደነበር የጠቀሱት ስራ አስኪያጇ አሁን ግን በሰራተኞች እጥረት ምክንያት ከሰባት ቶን በታች ለመሰብሰብ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

"በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌዎች መሰረት ስራችንን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እያከናወንን ቢሆንም ከፍተኛ የሰራተኛ እጥረት አጋጥሞናል" ያሉት ደግሞ የራያ ሆርቲካልቼር ባለቤት አቶ አማኑኤል አብርሃ ናቸው።

ሰራተኞች ባደረባቸው ስጋት ምክንያት ስራ በመልቀቃቸው በመስኖ የለማና በማሳ ላይ የሚገኝ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት  ለመሰብሰብ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ነው ባለሀብቱ የገለፁት።

በትግራይ ክልል የኢንቨስትመንትና ኤክስፖርት ኮሚሽን ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ማሳለጥና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ መሰለ የማነ በበኩላቸው ቫይረሱ በፈጠረው ጫና ምክንያት የሰራተኞችና የገበያ ችግር ማጋጠሙን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ባለሀብቶች ያጋጠማቸውን የሰራተኞች እጥረት ለመፍታት ከወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች በመተግባር በወረዳው የሚገኙ የቀን ሰራተኞች ለመተካት ጥረቱ ቀጥሏል ብለዋል።

ምርቶቻቸውን ከአሁን በፊት ወደ ጎረቤት ሃገራት ይልኩ የነበሩ ባለሀብቶች ደግሞ በመቀሌ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚሸጡበት መንገድ ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል።

ቶሎ የሚበላሹ አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚያመርቱ ባለሀብቶች በመቀሌ አሉላ አባነጋ ኤርፖርት የሚገኝ  የማቀዝቀዣ ቦታ ከኪራይ ነፃ በሆነ መንገድ ምርቶቻቸውን በቦታው እንዲያቆዩ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

የአግሮ ፕሮሰሲንግ የውጪ ምንዛሪ የሚገኝበት አንዱ የኢንቨስትመንት መስክ በመሆኑ የክልሉ ብሎም የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው ብለዋል ።

''ቫል ቬርዴ" የተባለው ካምፓኒ ባለፉት  23 ወራት ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጭ  በመላክ ለአገሪቱ 10 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጪ ምንዛሪ ማስገኘቱንም አቶ መሰለ በአብነት ጠቅሰዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም