ልማት ባንክ አስቸኳይ የብድር መስኮት ሊከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ልማት ባንክ አስቸኳይ የብድር መስኮት ሊከፍት ነው
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 22/2012 (ኢዜአ) የኢትዮያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ብድር መስጠት የሚያስችለውን አስቸኳይ የብድር መስኮት ሊከፍት መሆኑ ተገለጸ።
ለአምራች ህብረት ስራ ማህበራት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር ተዘጋጅቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዓለምዓቀፉ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የሚያስከትለውን የምጣኔ ሃብት ተጽዕኖ ለመቀነስ መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ከውሳኔዎቹ ውስጥም በተለይ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በቂ የብድር አቅርቦት ማመቻት አንዱ ነው።
ተቋማቱ የወረርሽኙን ተጽዕኖ ተቋቁመው ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩና ለሚያጋጥማቸው ችግር መፍትኤ ለመስጠት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተቋማቱ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አሰራር እንዲዘረጋ ማድረግ ደግሞ አንዱ የመፍትኤ አካል ነው።
''የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ብድር የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ በልማት ባንክ በኩል ያገኛሉ'' ብለዋል።
እንደ ዶክተር ኢዮብ ገለጻ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀጥተኛ ተጎጂ ያደረጋቸው የንግድ ተቋማት በየወሩ ይከፍሉት የነበረው የተጨማሪ እሴትና የተርን ኦቨር ታክስን አጠራቅመው ሰኔ ላይ እንዲከፍሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል።።
ውሳኔው ተቋማቱ በእጃቸው በቂ ገንዘብ እንዲኖርና የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።
የአምራች ህብረት ስራ ማህበራት ለህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማቅረብ የዋጋ ንረቱን በመቆጣጣር በኩል ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል።
ለዚህም ማህበራቱ አስፈላጊውን የብድር አቅርቦት የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
ምርቶቻቸውን ለውጪ ገበያ ብቻ እንዲያቀርቡ ግዴታ የተጣለባቸው በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ አምራቾች ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ ለሁለት ወራት በአገር ውስጥ ገበያ እንዲሸጡ ተፈቅዷል።
''ይህም የዓለም የገበያ ሁኔታ እስኪረጋጋ የአምራቾቹን ጉዳት ለመቀነስ ነው'' ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የጉምሩክ ኮሚሽን ተሰብሳቢ ዕዳ ያለባቸው ተቋማት ዕዳቸው እንዲሸጋገርና እንዲሰረዝ እንዲሁም በሽያጭ የተላለፉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያለባቸውን ዕዳ በአጭር ጊዜ ከፍለው ከጨረሱ ወለዳቸውና ቅጣታቸው እንዲነሳ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ዶክተር ኢዮብ ተናግረዋል።
በአሁን ጊዜ የመንግስት ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ወጪውም እየበዛ ቢሆንም የዜጎችን ህይወት ለመታደግና የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ውሳኔውን ማሳለፉን ገልጸዋል።
የንግድ ማህበረሰቡም ይህን ውሳኔ በመልካም በመውሰድ በሃላፊነት ስሜት የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል ጥሪ አቅርበዋል።