ቀጥታ፡

ከ20 ዓመት በታች የክልሎች ቼዝ ሻምፒዮና በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው

ድሬደዋ ሰኔ 27/2010 አራት ክልሎችና ሁለት ከተሞች የተካፈሉበት 2ኛው ከ20 ዓመት በታች የክልሎች ቼዝ ሻምፒዮና በድሬዳዋ ተጀመረ፡፡ ውድድሩ የቼዝ ስፖርትን ለማሳደግና የላቀ ችሎታ ያላቸው ለብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ  ቼዝ ፈደሬሽን ተናግሯል፡፡ ከትግራይ፤ ከአማራ፣ ከደቡብ ህዝቦች እና ከኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ የተውጣጡ 65 ሴትና ወንድ ስፖርተኞች በተናጠልና በጋራ ውድድራቸውን ትናንት ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ ለአንድ ሣምንት የሚቆየውን ውድድር መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከድር ጁሃር ውድድሩ የአእምሮ ብስለት የሚለካበትና እምቅ ችሎታቸውን ለመለየት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ በድሬዳዋ ቆይታቸው የርስ በርስ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸው ልምድና ባህል ለመለዋወጥም እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቼዝ ፈደሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ በላይነህ የቼዝ ስፖርት ለአእምሮ ብልፅግና ለትምህርት አቀባበል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል፤ ስፖርቱን በፕሮጀክት ሰልጣኞችና በታዳጊዎች እንዲዘወተር እየተሰራ እንደሚገኝና  በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ስፖርቱ የሚሰጥበት መንገድ ለማመቻቸትም ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ " ይህ ውድድር ለብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ጭምር የተወዳደሩበት በመሆኑ በርካታ ምርጥ ተጫዋቾችን በማፍራት ብሔራዊ ቡድናችንን አጠናክሮ በአፍሪካ ደረጃ ሀገራችንን ለማስጠራት ያግዛል" ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ቡድን ቼዝ አሰልጣኝ አቶ በቀለ ተስፋዬ በበኩላቸው ለስፖርቱ መጎልበት በህጻንነት የእድሜ እርከን ላይ መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል ስፖርተኛ ክብሮም በርሄ አምና ያገኘነውን ዋንጫ ዘንድሮም  ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሶ ውድድሩ ወግና ባህልን ለመካፈልና ለማካፈል ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥርና አንድነትን  የሚያጎለብት መሆኑን ገልጿል፡፡ " ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የካራቴ ውድድር ቡድናችን ያስመዘገበውን አኩሪ ውጤት በቼዝም ለመድገም ተዘጋጅተናል" ያለችው ደግሞ ዩሃና አለማየሁ የድሬዳዋ ተወዳዳሪ ናት፡፡ የአማራ ክልል ተወዳዳሪዋ ረድኤት ሰጠኝ በበኩሏ ባለፈው ውድድር ያገኘችውን የወርቅ ሜዳሊያ አሁንም ለመድገምና  ሀገሯን  በአለም  አቀፍ ውድድሮች በመወከል አሸናፊ መሆን እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡ "ቼዝ ለወጣቶች አእምሮ ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት እንደሌሎቹ ስፖርቶች ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብላለች፡፡ በመክፈቻ ዕለት በተካሄደው ውድድር በሴቶች ትግራይ ደቡብን ሶስት ለአንድ እንዲሁም  ኦሮሚያ ድሬዳዋን በተመሳሳይ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ ድሬዳዋ "ኤ" ቡድን ድሬዳዋ ቢን አራት ለባዶ ፣  ደቡብ አዲስ አበባን በተመሳሳይ ውጤት ሲያሸንፍ   ኦሮሚያ አማራን ሶስት ለአንድ  ረቷል፤ ውድድሩ ዛሬም ቀጥሏል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም