ቀጥታ፡

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በጋራ መቆምና መደጋገፍ ይገባል...ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 22/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በጋራ መቆምና መረዳዳት እንደሚገባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ አሳሰቡ።

ኢንጂነር እንዳወቅ ዛሬ ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች በአይነትና በገንዘብ የተደረገውን ድጋፍ ተቀብለው ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት አስቀድመው ለመከላከል የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የበርካታ አገራትን ቅስም የሰበረው የኮሮና ወረርሽኝ በሀገሪቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በጋራ መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአስተዳደሩ ማሕበራዊ ትረስት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ ነጋሽ በበኩላቸው እስካሁን በአስተዳደሩ በኩል 88 ሚሊዮን ብር፤ በአይነት ደግሞ 56 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተለግሷል ብለዋል።

በዛሬው እለትም ለሰባተኛ ጊዜ በተካሔደው የልገሳና የእውቅና ፕሮግራም የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በዚህ በከፋ ጊዜ ከሕዝብ ጎን መቆማቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል።

በዛሬው እለት ድጋፉን ካደረጉት ድርጅቶች መካከል ሰንሻይን ኮንስትራክሽን አንዱ ነው።

የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ድርጅቱ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የጽዳት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ቃለ ሒወት ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ 600 ሺህ ብር እና 50 አልጋዎች ያሉት የእንግዳ መረፊያ ለለይቶ ማቆያነት እንዲውል መለገሷን ጠቅሰዋል።

በዛሬው እለት ድጋፍ ያደረጉት ድርጅቶችና ተቋማት እነዚህን ጨምሮ ከ39 በላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም