ሁሉም ወገን በደም ልገሳ ሊሳተፍ ይገባል ... አቶ ርስቱ ይርዳው - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ወገን በደም ልገሳ ሊሳተፍ ይገባል ... አቶ ርስቱ ይርዳው
ሐዋሳ፤ ሚያዚያ 22/2012(ኢዜአ) ሁሉም ዜጋ በደም ልገሳ በመሳተፍ ሰብአዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ሊያሳይ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ጥሪ አቀረቡ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ትላንት ደም ለግሰዋል።
የክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ግብረ-ኃይል ሰብሳቢው አቶ ርስቱ ይርዳው በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለፁት በሀገር አቀፍ ደረጃ የደም ባንኮች ከፍተኛ የደም እጥረት አጋጥሟል ።
በክልሉም ተመሳሳይ ችግር መከሰቱን ገልፀው ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን "ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን ደም በመለገስ ሰብአዊ ወገንተኝነታችንን ማሳየት ይጠበቃል" ብለዋል።
መላው የክልሉ ህዝብና ኮሮናን በመከላከል ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ የሚገኙ በጎ ፍቃደኞች በደም ልገሳው በመሳተፍ አጋርነታቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል በየሶስት ቀኑ ተገናኝቶ ያከናወናቸውን ተግባራት በመገምገም የተጠናከረ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ አመራሩ ለክልሉ ህዝቦች ያለውን ፍቅርና አለኝታነት ለማሳየት ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።
ይህን ተግባራቸውን በየሶስት ወሩ አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አቶ ርስቱ ገልጸዋል።
የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ደም መለገስ ለከፍተኛ ጉዳትና ሞት የሚዳረጉ ወገኖችን ህይወት መታደግ ስለሆነ በዚህ ተግባር መሳተፋቸውን እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያዊነት መገለጫችን አንዳችን ለአንዳችን መድረስ ነው" ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በየደረጃው ያሉ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በአቅራቢያቸው ባሉ የደም ባንኮች እየተገኙ ደም በመለገስ ወገኖቻቸውን መታደግ ይገባቸዋል ብለዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሌሎች የጤና አገልግሎቶች ክፍተት እየተስተዋለባቸው እንደሆነ የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ የደም ልገሳው መቀዛቀዝም የዚሁ አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
ችግሩን ለማቃለልና መነቃቃት ለመፍጠር በዞንና ወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮችም በተመሳሳይ መልኩ በደም ልገሳው ለማሳተፍ መታቀዱን ተናግረዋል ፡፡
የሀዋሳ ደም ባንክ አስተባባሪ ወይዘሮ ብዙአየሁ በላቸው እንዳሉት ወረርሽኙን ተከትሎ የደም ለጋሾች ቁጥር በመቀነሱ በርካታ ህሙማን ለደም እጥረት መጋለጣቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ የደም ማሰባሰቡ ሥራ መሻሻል እየታየበት እንደሆነ ገልጸው ደም የሚያስፈልጋቸው በርካታ ወገኖች በመኖራቸው ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ልገሳውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።