የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ9 ወራት በዘመናዊ ግብይት ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የምርት ግብይት አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ9 ወራት በዘመናዊ ግብይት ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የምርት ግብይት አካሄደ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22 / 2012 (ኢዜአ) የአዳዲስ መጋዘኖችና የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ መከናወኑንም አስታውቋል።
ምርት ገበያው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ30 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በማገበያየት የእቅዱን 97 በመቶ ማሳካቱ ተገልጿል።
ከዚያም ባለፈ የአዳዲስ መጋዘኖችና የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ መከናወኑ ነው የተገለጸው።
በዘመናዊ የግብይት መድረክ 231 ሺህ 885 ቶን ቡና፣ 211 ሺህ 777 ቶን ሰሊጥ፣ 69 ሺህ 760 ቶን አኩሪ አተር፣ 46 ሺህ 914 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 39 ሺህ 286 ቶን ነጭ ቦሎቄና 3 ሺህ 201 ቶን ቀይ ቦሎቄ ማገበያየቱን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ክንውኑ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 20 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተመላክቷል።
በምርት ስብጥር ሲታይ የቡና ግብይት የዕቅዱን 99 በመቶ አሳክቷል።
የሰሊጥ ግብይቱ የዕቅዱን 75 በመቶ በማሳካት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በሀዋሳና በሁመራ በተቋቋሙት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት 987 ቶን ቡናና 6 ሺህ 665 ቶን ሰሊጥ ተገበያይቷል፡፡
የምርት ገበያው 23 ቅርንጫፎች ምርት የመረከብና ናሙና በመፈተሽ ደረጃ የመስጠት ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተገልጿል።
በዚህ መሰረት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 64 ሺህ ናሙና ተወስዶ ደረጃ ተሰጥቷል።
የአዳዲስ መጋዘኖች ግንባታ አፈጻጸም በቡሌ ሆራ 98 በመቶ፣ በመቱ 74 በመቶ፣ በቴፒ 80 በመቶ ደርሷል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ምርት ገበያው በዋናው መስሪያ ቤትና በሁሉም ቅርንጫፎች ሠራተኞችንና ተገበያዮችን በማሳተፍ የመከላከል ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ምርት ገበያው ኮሮናቫይረስ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን አገራዊ ጥረት ለማገዝ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር መለገሱን በመግለጫው አመላክቷል።