ስምንተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ስምንተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 ስምንተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ በስዊዘርላንድ ሉዛን ከተማ ይካሄዳል። የ2018 የዳይመንድ ሊግ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ውድድሮች በኳታር ዶሃ፣ በቻይና ሻንጋይ፣ በአሜሪካ ኢውጂን፣ በኢጣልያ ሮም እና በኖርዌይ ኦስሎና በስዊድን ስቶክሆልምና በፈረንሳይ ፓሪስ ተካሂደዋል። ነገ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ በስታድ ፒየር ዲ ኩበርቲን ስታዲየም በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ይሳተፋሉ። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ፣አትሌት በሱ ሳዶና አትሌት ዳዊት ስዩም ይካፈላሉ። አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር 11 ነጥብ በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን አትሌት በሱ ሳዶ 7 ነጥብ በማግኘት ስምንተኛ ደረጃን ላይ ተቀምጣለች። አትሌት ዳዊት ስዩም እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮች ነጥብ አላገኘችም። አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ የነገውን ውድድር ካሸነፈች ነጥቧን ወደ 19 ከፍ በማድረግ ወደ አንደኛ ደረጃ የመምጣት እድል አላት። የዳይመንድ ሊጉን በ14 ነጥብ የምትመራው የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ላውራ ሙር ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች። የኢትዮጵያ፣ኬንያና ሞሮኮ አትሌቶች ውድድሩን ለማሸነፍ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ-ገጹ አስፍሯል። በ800 ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሀብታም ዓለሙ ትሳተፋለች። አትሌቷ እሳከሁን ባደረገቻቸው የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች 16 ነጥብ ሰብስባ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አትሌት ሀብታም ባለፈው ሳምንት በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የ800 ሜትር ውድድር አራተኛ መውጣቷ የሚታወስ ነው። ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ካስተር ሴሜኒያ 24 ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን የነገውን ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቷታል። ነገ ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል የአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች ሩጫ ይጠበቃል። በውድድሩ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ሙክታር እድሪስ፣ሰለሞን ባረጋ፣አባዲ ሀዲስ፣ጌታነህ ሞላ፣ዳዊት ወልዴና ጥላሁን ሃይሌ ይሳተፋሉ። በአጭርና በመካከለኛ ርቀቶች እንዲሁም በአገር አቋራጭ ውድድሮች ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ5 ሺህ ሜትር ስምንት ነጥብ በማግኘት አንደኛ ደረጃን ይዟል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አባዲ ሀዲስ ስድስት ነጥብ በመያዝ ሶስተኛ አትሌት ዳዊት ወልዴ አንድ ነጥብ በማግኘት ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ሙክታር እድሪስና ሰለሞን ባረጋ የሚያደርጉት ፉክክር በአትሌቲክሱ አፍቃሪ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። ዘጠነኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በሞሮኮ ራባት ከተማ ይካሄዳል። በአፍሪካ፣ እስያና አውሮፓ ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በቤልጂየም ብራሰልስ ፍጻሜውን ያገኛል።