ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልልና በቤንች ሸኮ ዞን ክልከላውን የተላለፉ አሽከርካሪዎች ተቀጡ

ሀረር ፣ሚዛን ሚያዚያ 22 / 2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልልና በቤንች ሸኮ ዞን ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዘው የተላለፉ ክልከላዎችን የተላለፉ ከ300 በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጡ ።

የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዋና ዓቃቤ ህግ አቶ አዮብ አህመድ ዛሬ እንደገለፁት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የወጣውን አዋጅና ክልከላዎችን ጥሰው የተገኙ 200 አሽከርካሪዎችና የንግድ ተቋማት በገንዘብና በእስራት  እንዲቀጡ ተደርጓል ።

በፌዴራል መንግስት የወጣውን አዋጅና በክልሉ የተጣሉ ክልከላዎችን መሰረት በማድረግ በአቃቢ ህግና መርማሪ ፖሊሶች የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ህግን የማስፈጸም ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ።

ክልከላዎችን በመተላለፍ ከተፈቀደላቸው የሰው ቁጥር በላይ ያሳፈሩና ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ በማስከፈል ህብረተሰቡን ሲበዘብዙ የተገኙ 154 ታክሲዎች ከ1 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር በሚደርስ  ገንዘብ ተቀጥተዋል ።

ተደጋጋሚ ጥፋት ፈፅመው የተገኙ 9 ግለሰቦች ደግሞ ከ1 ዓመት ከ3 ወር እስከ 1 ዓመት ከ8 ወር በሚደርሰ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ዋና ዐቃቤ ህጉ ተናግረዋል።

ክልከላውን በመጣስ ህዝብን ሰብስበው ሲያገበያዩ የነበሩ፣ ሸቀጦችን ደብቀው የተገኙና ዋጋ ጨምረው የሸጡ 47 የንግድ ተቋማትም ከ2ሺ እስከ 15 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ ወረዳዎች ህገ ወጥ የመሬት ወረራና  የቤት ግንባታ የሚያከናውኑ ግለሰቦች መኖራቸውን ጠቅሰው ግብረ ኃይሉ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ከአቶ አዩብ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በቤንች ሸኮ ዞን ክልከላውን ተላልፈው የተገኙ 103 አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል ።

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ መከላከል ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ንጉሴ ታከለ ለኢዜአ እንደገለጹት ክልከላውን ተላልፈው የተገኙ 57 ባለሁለት እግር ሞተር ተሸከርካሪዎች፣ 19 ባለሦስት እግር ባጃጆች፣ 11 መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻና ቀሪዎቹ ደግሞ የጭነት ተሽከርካሪዎች ናቸው ።

አሽከርካሪዎቹ እንደ ጥፋታቸው ክብደት እስከ ሁለት ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ እንዲቀጡ መደረጉን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም