የሞጆ ሀዋሳ ፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 90 ኪሎ ሜትሩ በቀጣዮቹ 8 ወራት ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የሞጆ ሀዋሳ ፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 90 ኪሎ ሜትሩ በቀጣዮቹ 8 ወራት ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2012(ኢዜአ) ከሞጆ ሀዋሳ እየተገነባ ካለው የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 90 ኪሎ ሜትሩ (ከሞጆ ዝዋይ) በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፣ የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስልጣናት የሀዋሳ ሞጆ የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የአፈፃፀም ደረጃን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ከፕሮጀክቱ ግንባታ 90 ኪሎ ሜትሩ ማለትም ከሞጆ ዝዋይ ያለው በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
ከሞጆ እስከ ዝዋይ ያለውን የመንገድ ግንባታ የቻይና እና በኮሪያ ኩባንያዎች ተከፋፍለው እየሰሩት ያለ ፕሮጀክት ነው።
በመሆኑም የሞጆ መቂና የመቂ ዝዋይ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተለያየ ጊዜ የተጀመሩ ሲሆን የግንባታ ሂደቱ አሁን ላይ በቅደም ተከተል ከ90 እና ከ80 በመቶ በላይ ደርሷል።
ከዚህ አኳያ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በቀጣዮቹ ስምንት ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለኢዜአ ተናግረዋል።
መንገዱ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከአፈሩና መሬቱ ባህሪ ጋር እንዲጣጣምና በክረምቱ ወደ መንገዱ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ በበኩላቸው የፍጥነት መንገዶቹ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ባለፈ የትራፊክ አደጋን በሚቀንስ መልኩ የተሟላ የቴክኖሎጂና የጥራት ደረጃ እንዲኖራቸውም እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፍጥነት መንገዶች ግንባታ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ በመሆኑ በቀጣይነት በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ለማዳረስ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሞጆ መቂ ያለው ፕሮጀክት ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 7 ቢሊዮን ብር እና ከመቂ ዝዋይ ደግሞ ከኮሪያ ኢግዚም ባንክ በተገኘ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር አየተገነባ ያለ መሆኑ ይታወቃል።
የሞጆ ሀዋሳ 201 ኪሎ ሜትር የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የተጀመረው በ2008 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል።
የመንገዱ ግንባታም በአራት ምእራፍ ተከፋፍሎ እየተከናወነ ይገኛል።