ቀጥታ፡

በምርጫ ጉዳይ መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2012 (ኢዜአ) "ኮቪድ-19 ምርጫን ማራዘምና የህግ አማራጮች” በሚል ርዕስ መንግስት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ ልታካሂደው የነበረው የዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ ድንገት በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በመሆኑም በዛሬው እለት "ኮቪድ-19 ምርጫን ማራዘም እና የህግ አማራጮች” በሚል ርዕስ መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መክረዋል ።

በውይይቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በውይይቱ መክፈቻ ላይ፤ ፈታኝ አገራዊ ሁኔት ሲያጋጥም በመንግስት ከሚደረገው ውሳኔ በተጨማሪ ፓርቲዎች ያላቸውን ሀሳብ በማድመጥ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ውይይት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በዚህም በቀጣይ አገራዊ ምርጫ እጣ ፈንታ ላይ ፓርቲዎች መደረግ አለበት የሚሉትን ሀሳብ እንዲያካፍሉ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ውይይት መሆኑን አንስተዋል።

ለውይይቱ መነሻ ሃሳብም  ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ አራት ይዘት ያለው ጽሁፍ አቅርበዋል ።

ይህም መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮች፣ የመፍትሄ መስፈርቶችና ሂደቶች፣ አማራጮች እና ማጠቃለያ ያካተተ ይዘት ያለው ጽሁፍ ሲሆን በኮቪድ 19 ምክንያት ቀጣይ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ከህግ እና ከእውነታ አንፃር ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከህግ አንፃር አጠቃላይ ምርጫው እስከ ነሀሴ መጨረሻ መካሄድ እንዳለበት፣ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት እና በክልል ህገ-መንግስቶች ላይ እንደሚደነግግም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ከእውነታ አንፃር አጠቃላይ አገራዊ ምርጫውን እስከ ነሀሴ መጨረሻ ማካሄድ እንደማይቻል ተናግረዋል።

ለዚህም ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቀሰው ኮቪድ-19 አስፈላጊ የጥንቃቄ እርምጃዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ አገራዊ ትኩረት ወረሽኙን መመከት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ በመሆኑ ህግ እና እውነታ የሚጋጩ በመሆኑ እና ህገ-መንግስቱም ለዚህ ጉዳይ ግልጽና ቀጥተኛ መፍትሄ ያላስቀመጠ ሰለመሆኑ ተናግረው በዚህ ሳቢያ አገራዊ ቅርቃር ውስጥ መገባቱን ገልፀዋል።

መፍትሄ ለመፈለግ በተሄደው ርቀትም ሶስት የህግ ባለሙያዎች የምሁራን ቡድን መቋቋሙን እና ቡድኖቹ የተናጠልና የጋራ ምክክር አድርገው ሀሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

 ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በማያፋልስ መልኩ ችግሩን ለመቅረፍ አራት የመፍትሄ አማራጮች ማስቀመጣቸውን በመጥቀስ።

ይሄውም፤የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ህገ መንግስት ማሻሻል፣የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው።

አራቱም አማራጮች ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሰለመሆናቸው የተናገሩት ዶክተር ጌዲዮን ሁሉም ጠንካራና ደካማ ጎን ያላቸው ናቸው ብለዋል።

አገርና ህዝብን መታደግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ተባብሮ ኮቪድ -19 ን መመከት ያስፈልጋል በማለት ፓርቲዎች በመግባባት ህገ-መንግስታዊ ባህልን እንዲያዳብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም