ቀጥታ፡

አዲሱ የእግር ኳስ አመራር የእግር ኳሱ አጠቃላይ እድገት ላይ መስራት አለበት- ክለቦች

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ አመራር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አጠቃላይ እድገት አስተዋጽኦ ባላቸው ስራዎች ላይ ማተኮር እንዳለበት ክለቦች ገለጹ። ግንቦት 26 ቀን 2010ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንታዊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ተካሄዷል። አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር ከመደበኛ ስራዎች በበለጠ እግር ኳሱን በዘላቂነት ሊያሳድጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚገባው ኢዜአ ያነጋገራቸው ክለቦች ገልጸዋል። የኢትዮ-አሌትሪክ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሰ ኩሳ አዲሱ አመራር ካለፈው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር መማር የሚችለው ትልቁ ጉዳይ ከመደበኛ ስራዎች ይልቅ በአጠቃላይ የእግር ኳስ እድገቱ ላይ ማተኮር እንደሆነ ይናገራሉ። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመራበትን ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት የእግር ኳሱ ልማት ላይ መስራት እንዳለበትም ገልጸዋል። ለእግር ኳሱ እድገት መሠረታዊ የታዳጊዎች ስልጠና አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ለገሰ፤ ለዚህም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ጥራት ያላቸው የእግር ኳስ አካዳሚዎችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። አዲሱ አመራር በእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ትስስር እንዲጎለብት መግባባትና ሰላማዊ ግንኙነት ላይ ያተኮረ የቅንጅት አሰራር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትም ነው አቶ ለገሰ ያስረዱት። አመራሩ ያለውን ዝርዝር እቅድ አቅርቦ ከስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ለቀጣይ ስራዎች የሚያግዘውን ሀሳቦች ማግኘት እንደሚችል አክለዋል። የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል በበኩላቸው አዲሱ አመራር በባለሙያዎች የተደራጀና እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሚያካሄዳቸውን ውድድሮች አጠቃላይ የሚመራ አካል ማቋቋም ይገባዋል ነው የሚሉት። አዲሱ አመራር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት በዋነኛነት ትኩረት መስጠት እንደሚገባውና ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ሁሉንም ክለቦች በእኩል አይን ማየት እንዳለበትም ይናገራሉ። በእግር ኳስ ልማቱ ረገድ አዲሱ አመራር ውድድር የሚካሄድባቸውን ስታዲየሞችን ደረጃና ጥራት በመገምገም ውድድር ለማካሄድ የማይመጥኑ ሜዳዎችን ማገድ እንደሚገባውም ተናግረዋል። የአንድ እግር ኳስ እድገት ማሳያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ ስታዲየሞች መሆናቸውንና በዚህም ረገድ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለስታዲየሞች ጥራትና ደረጃ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ውድድር ቻን ከወዲሁ እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞች ዓለም አቀፍ ደረጃቸው በባለሙያዎች ሊገመግም እንደሚጋም ነው አቶ አብነት ያስረዱት። በአሁኑ ሰዓት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው የእግር ኳስ ሜዳ ላይ እየታየ ያለው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት የስፖርቱን እድገት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ፌዴሬሽኑ አስችኳይ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበትና ለዚህም በቁርጠኝነት መስራት እነዳለበት ገልጸዋል። "አዲሱ አመራር በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ባይችል እንኳ ለእግር ኳሱ እድገት መሰረት መጣል የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት አለበት" የሚሉት ደግሞ የመከላከያ ስፖርት ክለብ ዳይሬክቶሬት ሃላፊ ተወካይ ኮሎኔል ንጉሴ አየለ ናቸው። ምርጫው ሰዎችን በሰዎች መተካት ሆኖ እንዳይቀር አዲሱ አመራር የተዳከመውን እግር ኳስ ለመታደግ በቁርጠኝነትና በትጋት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል። አመራሩ በምርጫው ላይ ተፎካካሪ የነበሩ ግለሰቦችን እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበረውን የፌዴሬሽን አመራር ስራዎች በመገምገም እንደ ግብዓት መውሰድ እንዳለበት አመልክተዋል። አዲሱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ከሰባት ወር ቆይታ በኋላ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም የጀመረው ጥረት መልካም የሚባል እንደሆነና የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ምርጫ ሁሉንም በተለያየ ደረጃ የሚካሄዱ ውድድሮችን ያማከለ መሆን አለበት ብለዋል። ክለቦችም ለእግር ኳሱ አድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም