በአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል 188 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል 188 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ተሰበሰበ
ባሀር ዳር (ኢዜአ) ሚያዚያ 21/2012 በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ 188 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት መሰብሰቡን የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
ግብረ ኃይሉ አባልና የገቢ አሰባሰብ ዘርፍ ሰብሳቢ ዶክተር ጥላሁን ማህሪ ለኢዜአ እንደገለፁት የሃብት አሰባሰቡ ስራ ተቋማት፣ ባለሃብቱና ሌሎችን ግለሰቦች በማስተባበር እስከ ወረዳ አደረጃጀት በመፍጠር እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም 68 ሚሊዮን 900ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ እና ከ119 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ደግሞ በዓይነት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
ከተሰበሰበው ሃብት ውስጥም ከፊሉን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ቀሪው ሀብት የቫይረሱ ስርጭት ለመከላከል ለመጠባበቂያነት የተያዘ ነው።
"የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ቀጣይ ሁኔታ ለመተንበይ ያስቸግራል " ያሉት ዶክተር ጥላሁን አሁንም የሃብት ማሰባሰብ ስራው መቀጠሉን ተናግረዋል።
ኮሮናን ከመከላከሉ በተጓዳኝ የክልሉ ምጣኔ ሀብት አቅም ውስን መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ምጣኔ ሀብቱን በዘላቂነት ለመደገፍም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ዶክተር ጥላሁን ጨምረው ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በወልድያ ከተማ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በቀበሌ ደረጃ የምግብ እህል በማሰባሰብ የማከማቸት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የግብአት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተገኘ ፈንታው አስታውቀዋል።
በቅርቡም ቤት ለቤት በመዘዋወርም 360 ኩንታል የምግብ እህል መሰብሰቡን አመልክተው ሁለት ሺህ 648 እሽግ ፓስታ እና 601 ሊትር የምግብ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መገኘቱን ጠቁመዋል።
በከተማ አስተዳደሩ እስካሁን በተደረው ጥረት ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል በማሰባሰብም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሁለት ሺህ 200 ሰዎች ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።